በቴክኖሎጂው ዓለም ተወዳዳሪ ሙያተኞችን የማፍራት ጥረት

You are currently viewing በቴክኖሎጂው ዓለም ተወዳዳሪ ሙያተኞችን የማፍራት ጥረት

የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (የሰው ሰራሽ አስተውሎት) ልማት ግስጋሴ የዓለምን ስርዓት በከፍተኛ ፍጥነት እየለወጠው ይገኛል፡፡ እያንዳንዱ የስራ ዘርፍ በቴክኖሎጂ እየተደገፈ ወደ ዲጂታላይዜሽን ስርዓት እየተሸጋገረ ስለመሆኑ ዕለት ተዕለት በሚደረገው እንቅስቃሴ መገንዘብ ይቻላል።

አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኮምፒውተሮች የተለያዩ የተሻሻሉ ተግባራትን እንዲያከናውኑ የሚያስችል የቴክኖሎጂ ስብስብ ሲሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ንግዱ፣ ግብርናው፣ ህክምናው፣ ቱሪዝሙ፣ ማኑፋክቸሪንጉ፣ ትራንስፖርቱ፣ የጦርነት አውድማው፣ የደህንነት ተግባራት ሁሉ በዚህ ስርዓት የተቃኙ እንዲሆኑ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው፡፡ በተጨማሪም ቋንቋ መተርጎም፣ መረጃ መተንተን፣ ጥቆማዎችን መስጠት እና ሌሎችን ተግባራትንም ያካትታል፡፡

በጥቅሉ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የወቅቱ የዓለም ቋንቋ እስከመሆን ደርሷል፤ የፉክክር መድረክም ሆኗል። የወደፊቱን የዓለም ስርዓት የሚበይን እና ሁለንተናዊ እንቅስቃሴውንም በዚያ ቅኝት ውስጥ ወደመምራት እየሄደ እንደሆነም ይነገራል። ዘርፉ በዓለም ዙሪያ በሰዎች የሚሰሩ 300 ሚሊዮን የሚደርሱ ሥራዎችን ሊተካ እንደሚችል ቴክኖሎጂ ኢን ዘ ኒው ኢራ የተሰኘ ገፀ ድር ላይ እ.ኤ.አ በ2024 የወጣ መረጃ ያመላክታል፡፡

ታዲያ ኢትዮጵያ በዚህ አዲስ ስርዓት ውስጥ ተሳትፎ በማድረግ የጥቅሙ ተጋሪ እንድትሆን ምን ዝግጅት እያደረገች ነው? በቅርቡ የተጀመረውና በሀገር ደረጃ በሶስት ዓመታት ውስጥ 5 ሚሊዮን ወጣቶችን ለማሰልጠን ተወጥኖ የተገባበት የኮደርስ ኢንሼቲቭ በዚህ ረገድ የሚኖረው አበርክቶስ ምን ይሆን?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አምስት ሚሊዮን ዜጎች የዲጂታል ቴክኖሎጂ ስልጠና ተጠቃሚ የሚሆኑበትን “አምስት ሚሊዮን የኢትዮጵያ ኮደሮች ኢንሼቲቭ”ን ባስጀመሩበት ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ በአሁኑ ፈጣን ዓለም ባላሰለሰ ትምህርት እና የክህሎት እድገት ውስጥ መሳተፍ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ እጅግ አስፈላጊ ሆኗል ማለታቸው ይታወሳል።

“ራሳቸሁን በእውቀት በመገንባት በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ በጎ ተፅዕኖ ለመፍጠር ለምትጓጉ ሁሉ የአምስት ሚሊዮን ኮደርስ ፕሮጀክት ቀዳሚ ሊያደርጋችሁ ተሰናድቶላችኋል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ “የትምህርት እና የእውቀት መነሻችሁ እና ያላችሁበት ደረጃ ምንም ይሁን ያላችሁን ክህሎት ለማሳደግም ሆነ አዲስ ነገር ለማወቅ ለምትሹ ሁሉ ሰፊ የእድል በር ተከፍቶላችኋል፡፡ በመላው ኢትዮጵያ ያላችሁ የክህሎት አበልፃጊዎች፣ አሳዳጊዎች፣ ዩኒቨርሲቲዎች ይኽንን ፕሮጀክት እና እንቅስቃሴዎቹን እንዲደግፉ ጥሪ አቀርባለሁ” ብለው ነበር።

የ“አምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ’’ መርሃ ግብር በኢትዮዽያ እና በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መንግሥታት የተጀመረ የዲጂታል ሥራ ክህሎቶችን የማሳደጊያ የትብብር ፕሮጀክት ሲሆን፣ በማደግ ላይ ባለው ዲጂታል ኢኮኖሚ ከባቢ የመጪው ትውልድ ኢትዮጵያዊያንን ለማብቃት ታልሞ የተጀመረ ስለመሆኑ ተገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ ኢንጂኒየር ሰለሞን አማረ ከ2017 ዓ.ም እስከ 2019 ዓ.ም ድረስ በመርሃ ግብሩ 5 ሚሊዮን ኮደሮችን ለማሰልጠን ተወጥኖ እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቁመው፣ በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃም በሶስት ዓመታት ውስጥ 300 ሺህ ዜጎች ሥልጠናውን ወስደው ለምርቃት እንዲበቁ ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን ገልፀዋል፡፡

የ“አምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ” መርሃ ግብር ሐምሌ 16 ቀን 2016 ዓ.ም መጀመሩን ያወሱት ኢንጂኒየር ሰለሞን፣ በ2017 ዓ.ም መጨረሻ 75 ሺህ ዜጎችን በአንድ ወይም ከአንድ በላይ በሆኑ የስልጠና ዘርፎች በሰርተፊኬት ለማስመረቅ ተወጥኖ እየተሰራ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ 4 ኮርሶች እየተሰጡ መሆኑን ጠቁመው፣ እስከ አሁን ባለው ጊዜ ውስጥ በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ በፕሮግራሚንግ ፈንዳሜንታል ከ45 ሺህ በላይ፣ በዳታ አናሊሲስ ፈንዳሜንታል 51 ሺህ በላይ፣ በአንድሮይድ ደቨሎፕመንት 49 ሺህ፣ ዘግይቶ በተጀመረው አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ደግሞ ከ18 ሺህ በላይ በጥቅሉ 165 ሺህ 99 ዜጎች በአራቱም የስልጠና ዘርፎች ስልጠናውን እየተከታሉ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

ከእነዚህ ሰልጣኞች መካከል 55 ሺህ 886 ሰልጣኞች ስልጠናውን አጠናቅቀው ሰርተፊኬት ወስደዋል፡፡ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም 75 ሺህ ሰልጣኞች ሰርተፊኬት ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል ሲሉም አክለዋል፡፡

ስልጠናውን ከወሰዱ ዜጎች መካከል በዘርፉ ውጤታማ ስራ የሰሩ ስለመኖራቸውም ተናግረዋል፡፡ ለአብነትም የአዲስ አበባ ከተማ ሲቪል ምዝገባና የነዋሪዎች አገልግሎት ኤጀንሲ 256 ሰዎችን የ“አምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ’’ አሰልጥኖ አስመርቋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ብዙዎቹ ሁለትና ሶስት ሰርተፊኬት የወሰዱ ናቸው። በስልጠናው የተሳተፉ እነዚህ ዜጎች የተቋሙን የስራ አፈፃፀም አሻሽለውታል። የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ፣ የአዲስ አበባ ስራና ክህሎት ቢሮ፣ የካ፣ አዲስ ከተማ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ ቂርቆስ፣ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተሞችም ሰራተኞቻቸው ስልጠናውን እንዲወስዱ እያደረጉ ነው፡፡ አፈፃፀማቸውም በዚያው ልክ እያደገ ነው ብለዋል፡፡

እንደ ኢንጂኒየር ሰለሞን ገለፃ፣ ከመንግስት ተቋማት ውጭ ያሉ ወጣቶችም ከ“አምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ” ስልጠና በኋላ የተለያዩ ፕሮግራሞችን እያለሙ ይገኛሉ፤ ያለሟቸውን ፕሮግራሞች ይዘው ወደ አዲስ አበባ ከተማ ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ በመምጣት መዝግቡልኝ ብለው የሚጠይቁ አሉ፡፡ ለአብነትም አንድ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የሚኖር ግለሰብ አራቱንም ኮርሶች አጠናቅቆ ሶስት የተለያዩ ሲስተሞችን አልምቶ ወደ ተግባር አስገብቷል። የራሳቸውን ስታርት አፕ አቋቁመው የተሻለ ህይወት በመምራት ላይ የሚገኙም አሉ፡፡

የግል የአይሲቲ ተቋማት በእነዚህ ኮርሶች ውስጥ ያለፉ ሰልጣኞችን በቅጥር እንድናቀርብላቸው እየጠየቁ ነው ያሉት ኢንጂኒየር ሰለሞን፣ በተለይ በሶፍት ዌር ስልጠና ዘርፎች ሰርተፊኬት ያላቸው ዜጎች ተፈላጊ ሆነዋል፡፡ ይህም በመንግስት ተቋማት ያሉ ሰራተኞች በቴክኖሎጂ ራሳቸውን ማብቃት እንዳለባቸው አመላካች ነው፡፡

የ“አምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ” ሰልጣኞች ለዝግጅት ክፍላችን ባጋሩት ሀሳብ የዲጂታላይዜሽኑን ዓለም ለመቀላቀልና በዓለም አቀፍ መድረኮች ተወዳዳሪ ለመሆን ቀላል የማይባል ክህሎት መቅሰማቸውን ተናግረዋል። ተማሪ ሶፎንያስ ወዳጄ ሀሳባቸውን ካጋሩን ሰልጣኞች መካከል አንዱ ነው። ወጣቱ በክረምቱ ወቅት ፕሮግራሚንግ ፈንዳሜንታልስ (Programming Fundamentals) እና አንድሮይድ ደቨሎፐር ፈንዳሜንታልስ (Android Developer Fundamentals) የተሰኙ ኮርሶችን ወስዶ በማጠናቀቅ ሰርተፊኬት መውሰዱን ነግሮናል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ የሆነው ሶፎንያስ እነዚህን ኮርሶች በመውሰዱ ከዚህ ቀደም በጉዳዩ ላይ ከነበረው መረዳት ጋር ተዳምሮ የተሻለ ዕወቀት እንዳገኘበት ተናግሯል፡፡ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ የሶፍት ዌር ኢንጂነሪንግ ዘርፍን ለመቀላቀል ትልቅ እገዛ እንዳበረከተለትም ጠቁሟል፡፡

ሌላው የ“አምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ” መርሃ ግብር ተካፋይ ተማሪ ቃልአብ ነጋ ይህን ዕድል ማግኘቱ በህይወቱ ላይ ትርጉም ያለው ልዩነት ማምጣቱን ይናገራል፡፡ ወጣቱ የፕሮግራሚንግ ፈንዳሜንታልስ (Programming Fundamentals) እና የአንድሮይድ ደቨሎፐር ፈንዳሜንታልስ (Android Developer Fundamentals) ኮርሶችን ወስዶ ሰርተፊኬትም አግኝቷል።

ሥልጠናው ወደፊት የሚያስበውን ለማሳካት የሚያስችለውን ክህሎት በቀላሉ ለመረዳት የሚያችስል መሆኑን ቃልአብ ገልጿል። የዚህ ክህሎት ባለሙያ መሆን ተወዳዳሪነትን የሚጨምርና ተፈላጊነትን የሚያሳድግ በመሆኑ በተገኘው ዕድል ደስተኛ መሆኑን ጠቁሟል። “ስልጠናው በኦንላይን የሚሰጥ በመሆኑ በፈለግኩበት ጊዜ ለመሰልጠን አስችሎኛል” የሚለው ቃልአብ፣ የጊዜ ገደብ ሳይኖርበት በየትኛውም ሰዓትና ቦታ ሆኖ የእጅ ስልኩን ተጠቅሞ ስልጠናውን መከታተል መቻሉን ተናግሯል፡፡ 

ወጣቱ እንደገለጸው፣ ይህ ለወጣቶችም ለሀገርም ትልቅ ዕድል ነው፡፡ ምክንያቱም ማንኛውም ሰው ተምሮ ሲጨርስ ህጋዊ ሰርተፊኬት ያገኛል፡፡ ይህ ደግሞ ዓለም ዓቀፍ ተወዳዳሪ ያደርገዋል። በመሆኑም በየትኛውም አካባቢ ያሉ ወጣቶች በዚህ የሙያ ዘርፍ ተወዳዳሪ ብሎም ተጠቃሚ ለመሆን ተመዝግበው መማር እንዳለባቸው መክሯል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ የተሻለ የቴክኖሎጂ ክህሎት ያላቸው ግለሰቦች እንደመኖራቸው መጠን በዚህ ስልጠና ውጤታማ የመሆን ዕድል  አለ፡፡ ሰልጣኞቹ ሰርተፊኬት የማግኘት ዕድል ስላላቸው በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ እንዲሳተፉ በር ይከፍትላቸዋል፡፡

የከተማዋ ወጣቶች የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ከተለያዩ ተቋማት ጋር ተባብሮ እየሰራ እንደሚገኝ ከቢሮው ያገኘናቸው መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ ለአብነትም ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር ጠንካራ ትብብር አለው፡፡ በተጨማሪም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ከአዲስ አበባ ስራ እና ክህሎት ቢሮ፣ ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ እና ሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በትብብር እየተሰራ ነው፡፡

በተካልኝ አማረ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review