የመዲናዋ  ኪነ-ጥበባዊ ዝግጅቶች

You are currently viewing የመዲናዋ  ኪነ-ጥበባዊ ዝግጅቶች

ዛሬ እና ነገን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናት በመዲናችን አዲስ አበባ የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ መሰናዶዎች ይካሄዳሉ፡፡  ከእነዚህ መሰናዶዎች መካከል አዳዲስ የመጻሕፍት ምርቃትና ህትመት፣ የሥዕል ዓውደ-ርዕይ፣ ቴአትሮች፣ ኪነ ጥበባዊ ውይይቶች እና ሌሎችም ይገኙበታል። ለመረጃ ይሆንዎት ዘንድ የአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍል መርሃ ግብሮቹን እንደሚከተለው አዘጋጅቷቸዋል፡፡

የመጽሐፍ ምርቃት

በዛሬው ዕለት “ስሜ ደበላ፤ ታላቁ የግብርና ምርምር ሥርዓት መሪ” የተሰኘው መጽሐፍ ይመረቃል፡፡ በግብርና ምርምር ተቋም መሥራች፣ አደራጅ እና መሪነታቸው የሚታወቁትን የዶ/ር ስሜ ደበላን አበርክቶዎች የሚዘክረው እና በደራሲ ገስጥ ተጫኔ የተጻፈው ይህ መጽሐፍ በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ይመረቃል። በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ የዶ/ር ስሜ ደበላ ሕይወት እና አበርክቶዎች በተለያዩ ዝግጅቶች ይዘከራሉ። መርሃ ግብሩ ጠዋት ከ3፡00 ሰዓት ጀምሮ ይደረጋል ተብሏል፡፡

በሌላ መረጃ “ኀልዮት” የተሰኘ አዲስ መጽሐፍ ለንባብ በቅቷል፡፡ በጋዜጠኛና ደራሲ ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ የተዘጋጀው ይህ መጽሐፍ ወደ 25 ዓመታት በቆየበት የጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ ቃለ መጠይቅ ያደረጋቸው ታዋቂ ሰዎች ተካትተውበታል፡፡ 19 ቃለ ምልልሶችን “ኀልዮት” በሚል ርዕስ ለንባብ ያበቃው ደራሲና ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ፣ ከትዕግሥት ዋልተንጉሥ ጋር ሆኖ የጻፈውንና በ7 ወር ውስጥ  7ኛ ዕትም ላይ የደረሰውን “ምን ሆኛለሁ?” መጽሐፍ ጨምሮ “ኅልዮት” 8ኛ መጽሐፉ ነው። 6ቱ መጽሐፍት “ፍልስምና” በሚል ርዕስ ያዘጋጃቸውና ያሳተማቸው ናቸው።

መጽሐፉ 19 ኢትዮጵያውያን አሳቢዎች በቃለ መጠይቅ ቅርጽ ለሀገር እና ለተነሳው እውነት “ይበጃል” ያሉትን የሰጡበት ነው። አሳቢዎቹ በአርበኝነት፣ በፍልስፍና፣ በፖለቲካ፣ በዲፕሎማሲ፣ በኪነ-ጥበብ፣ በታሪክ፣ በሥነ-ጽሑፍ፣ በአዕምሮ ጤና፣ በአስተዳደር፣ በጋዜጠኝነት፣ በንግድ እና በመሳሰሉት የሄዱባቸውን መንገዶች የሚያሳይ ነው ተብሏል።

በሌላ መረጃ፣ ፍካሬ የተሰኘው አዲስ መጽሐፍ ለንባብ ሊበቃ ነው፡፡ እመጓ፣ ዝጎራ፣ መርበብት፣ ሰበዝ፣ ሚተራሊዮን በተሰኙት መጻሕፍቱ እጅግ ዝናን ያተረፈው ደራሲና ተመራማሪ ዓለማየሁ ዋሴ “ፍካሬ” የተሰኘው አዲስ መጽሐፍ በሚቀጥለው ሳምንት መጀመሪያ ለንባብ እንደሚበቃ ታውቋል፡፡ መጽሐፉ በብራና መጽሐፍት መደብርና በሌሎችም ማከፋፈያዎች አንባብያን ያገኙታል ተብሏል፡፡

በሌላ መረጃ አንጋፋው ሃያሲና ደራሲ አስፋው ዳምጤን የሚያከብር መርሃ ግብር የፊታችን ረዕቡ መጋቢት 10 ቀን 2017 ዓ.ም ይቀርባል፡፡ በዚህ መርሃ ግብር ሃያሲና ደራሲ አስፋው ዳምጤ ለኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ፣ እንዲሁም በጥበብ ስራዎቻቸው ዙሪያ መነሻ ጽሑፎች ይቀርባሉ፡፡ በዕለቱ ታዋቂ የኪነ ጥበብ ሰዎች በሃያሲና ደራሲ አስፋው ዳምጤ ህይወትና ስራዎች ላይ ምስክርነት ይሰጣሉ ተብሏል፡፡ ዝግጅቱ የሚቀርበው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ቤት በ7፡30 ሰዓት ይጀምራል ተብሏል፡፡ 

ሥዕል

‘የደራሲው ስዕል’ የተሰኘው የስዕል አውደ ርዕይ በመታየት ላይ ነው፡፡ ባለፈው ሰኞ ዕለት በይፋ የተከፈተው ይህ የስዕል አውደ ርዕይ የተለያዩ የጥበብ ሥራዎች የቀረቡበት ነው ተብሏል፡፡ በሰዓሊ ምዕራፍ ግሩም የተሳሉ ስዕሎች የቀረቡበት ይህ አውደ ርዕይ ሃያት ሬጀንሲ ሆቴል በሚገኘው ፈንድቃ  የባሕል ማዕከል እስከ ፊታችን ሰኞ መጋቢት 15 ቀን 2017 ዓ.ም ለእይታ ይቆያል ተብሏል።

የቴአትር መርሃ ግብር

በመዲናችን አዲስ አበባ ቅዳሜ እና እሁድ ከሚታዩ ቴአትሮች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡ ባሎች እና ሚስቶች የተሰኘው ቴአትር ቅዳሜ 8:00 ሰዓት በብሔራዊ ቴአትር ቤት ይታያል። 11፡30 ደግሞ ባቡሩ የተሰኘው ቴአትር በዚያው በብሔራዊ ቴአትር ይታያል። እሁድ በ8፡00 ሰዓት ሸምጋይ ቴአትር ለእይታ የሚቀርብ ሲሆን፤ እምዬ ብረቷ የተሰኘው ቴአትር ደግሞ 11፡30 ላይ ይታያል፡፡ እንዲሁም ሐሙስ ቀን 11:30 ጎዶ’ን ጥበቃ፣  አርብ በ11፡30 የሕይወት ታሪክ በብሔራዊ ቴአትር ቤት ይታያሉ፡፡ አርብ በ12፡00 ሰዓት ደግሞ ዋዋጎ በዓለም ሲኒማ ለጥበብ አፍቃሪያን ለዕይታ ይቀርባል፡፡

በአብርሃም ገብሬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review