ልጆችዬ እንዴት ናችሁ? ትምህርት ጥሩ ነው? መልሳችሁ፤ “አዎ” እንደሚሆን አምናለሁ፡፡ ልጆችዬ፤ “የእናት ፍቅር፣ የጓደኛ ፍቅር፣ የሀገር ፍቅር” ሲባል በተደጋጋሚ ሰምታችኋል ብዬ አስባለሁ። ዛሬ በብዙ ዓይነት ከሚገለፀው ፍቅር መካከል፤ “የሀገር ፍቅር መገለጫዎቹ ምንድን ናቸው?” የሚለውን እንመለከታለን፡፡ “ለእናንተ የሀገር ፍቅር ምንድን ነው፤ በምንስ ይገለፃል?” ልጆችዬ፤ በጥያቄው መሰረት የራሳችሁን መልስና አስተያየት ሰጣችሁ አይደል፤ ጎበዞች፡፡ አሁን ደግሞ፤ ያነጋገርናቸው ተማሪዎች ስለ ሀገር ፍቅር የሰጡትን ሃሳብ እናካፍላችሁ፡፡

ትንሳኤ ዜና ትባላለች፡፡ የሳውዝ ኢስት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ9ኛ ክፍል ተማሪ ነች፡፡ “ከሀገር ፍቅር መገለጫዎች አንዱ ያለንን ሀብት መጠበቅ ነው። ለምሳሌ፡- የተፈጥሮ ሀብቶቻችንን በመጠበቅ እና ቅርሶችን በመንከባከብ ለሀገራችን ያለንን ፍቅር መግለጽ እንችላለን፡፡ ትምህርታችንን እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ተምረን፣ በተማርነው ትምህርት ከራሳችን አልፎ ቤተሰቦቻችንን ለማገዝ፣ ሀገራችንን ለመለወጥ ከተጠቀምንበት ይህም ሌላኛው የሀገር ፍቅር መገለጫ ነው ማለት ነው” ብላለች፡፡
በትምህርት ቤቱ የ9ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ጺዮን አለማየሁ በበኩሏ፤ ሀገር እና እናትን በማነፃፀር ፍቅሯን ገልፃለች፡፡ “ሀገር እናት ማለት ናት፡፡ እናት እንጀራ ጋግራ የምታበላ ስትሆን ሀገር ደግሞ እንደ ጤፍ የመሳሰሉ ለመኖር አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን አፍርታ ታቀርብልናለች። የሀገር ፍቅር መገለጫው ሀገርን መውደድ ማለት ነው። ለሀገራችን የቻልነውን ሁሉ ማድረግ ነው ፡፡ ለምሳሌ፡- ሀገር ልማት፣ ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነት ትፈልጋለች። ለዚህ ደግሞ ሁላችን መተሳሰብና መረዳዳት ይገባናል። ወደፊት ተምረን ውጤታማ በመሆን ሀገራችንን መጥቀምም ይኖርብናል” ስትል አብራርታለች፡፡

ልጆች፤ ከላይ የተነሱት ሀሳብ ትክክል ነው። ለመጨመር ያህል የሀገር ፍቅር የተወለድንባትን፣ ያደግንባትን፣ የምንማርባትን፣ የምንኖርባትን ሀገር የእኛ አድርጎ ከማሰብ ይጀምራል። የሀገር ፍቅር፤ ለሀገርና ለወገ የሚጠቅሙ ተግባራትን በመስራት የሚገለጽ የፍቅር አይነት ነው።
የሀገር ፍቅር ከቤተሰብ ይጀምራል። ቤተሰቡን፣ ጎረቤቱን፣ አካባቢውን እያለ ወደ ሀገር ይሸጋገራል፡፡ ይህ የሚገለጸው ሁሉም በተሰማራበት ሙያ፣ ባለው እውቀትና ልምድ እንዲሁም በሀቀኝነት ህዝቡን በማገልግል ነው፡፡ ለምሳሌ፡- አንድ ነጋዴ ሀገሩን የሚወድ ከሆነ ግብር በታማኝነት ይከፍላል። ተማሪውም ሀገሩን ወደደ የሚባለው በትክክል ትምህርቱን ሲከታተል ነው። ምክንያቱም
ተምሮ እውቀት ሲኖረው ነው ራሱንና ቤተሰቡን ከመጥቀም ባለፈ ሀገሩን የሚጠቅመው፡፡
በዓድዋው ጦርነት ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የታጠቀውን የጣሊያንን ወራሪ ኃይል በጎራዴና ቀላል መሳሪያዎች ድል መንሳት የሀገር ፍቅር ማሳያ ነው። አሁን ላይ ደግሞ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ የታየው መነሳሳት ሌላው ሀገር ፍቅር መገለጫ ነው። የሀገር ፍቅር ሀገር ለመገንባትና ለመጠበቅ ከፍተኛ ድርሻ አለው፤ እሺ ልጆችዬ፡፡
የሀገር ፍቅር ከራስ ጥቅም ይልቅ የህዝቡን ጥቅም ማስቀደም፤ ከማጭበርበር ይልቅ ለፍትሃዊነት ተገዥ መሆን ነው። የሀገር ፍቅር ለህዝብ ጥቅም ሲባል ከራስ ወዳድነት መራቅን ይጠይቃልና ሁሉም በተሰማራበት የግል ጥቅሙን ወደጎን በመተው፣ የሀገሩንና የህዝቡን ጥቅም በማስቀደም ፍቅሩን ማሳየት ይኖርበታል፡፡ የሀገር ፍቅር ዕለት ከዕለት የምንኖረው ህይወታችን ሊሆን ይገባዋል፡፡
ልጆችዬ፤ እናንተም በትምህርታችው ጎበዝ በመሆን ሀገራችሁንና ማህበረሰባችሁን የሚጠቅም ስራ ላይ ለመሰማራት ከወዲሁ መጣር አለባችሁ።
ሀገራችሁን የሚያስጠራ እና ለዓለም ማህበረሰብ የሚያስተዋውቅ ስራ በመስራት ባንዲራዋ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ማድረግ ይጠበቅባችኋል፡፡
በለይላ መሀመድ