አንጋፋው የዴሞክራሲ ስርዓት…

You are currently viewing አንጋፋው የዴሞክራሲ ስርዓት…

AMN-መጋቢት 5/2017 ዓ.ም

ዓለም በይስሙላ ዴሞክራሲ በሚሰቃይበት ወቅት የገዳ ሥርዓት ግን ለዘመናት ያበጀውን የሥልጣን መዋቅር ሳያዛንፍ በየ8 ዓመቱ ለተተኪው ሥልጣኑን ያስረክባል።

የገዳ ሥርዓት ዘመናዊውን ዴሞክራሲ የቀደመ ታሪክ ያለው እና የኦሮሞ ህዝብ ለክፍለ ዘመናት ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን የሚያስተዳድርበት ሀገር በቀል እሴት ነው።

በሥርዓቱ ምላሽ የማያገኝ ችግር አይኖርም።

ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እና ለዘላቂ ሠላም ያለው አስተዎፅዖም በእጅጉ የላቀ ነው።

ዩኔስኮ ይህ ድንቅ እሴት ለዓለም የሚያበረክተውን ትልቅ ጥቅም ከግንዛቤ በማስገባት በፈረንጆቹ 2016 በዓለም የማይዳሰስ ቅርስነት መመዝገቡ ይታወሳል።

ከሰሞኑ የተካሄደውን 72ኛው የቦረና ገዳ ባሊ (ሥልጣን) ርክክብን አስመልክተው የውጭ መገናኛ ብዙሀን ‘ጠንካራው ባህላዊ የዴሞክራሲ ሥርዓት’ ሲሉ ዘግበውታል።

በሥነ ሥርዓቱ 71ኛው የቦረና አባ ገዳ ኩራ ጃርሶ ለ72ኛው አባ ገዳ ጉዮ ቦሩ ጉዮ ሥልጣን ያስረከቡበት ነበር ።

ሽግግሩ በየ8 ዓመቱ ያለ ምንም እንከን የሥልጣን ዘመኑን ካጠናቀቀው አባ ገዳ አዲስ ሥልጣን ወደ ሚረከበው አባገዳ የሚተላለፍ መሆኑን አይ ላቭ አፍሪካ ጽፏል።

ይህ ሥርዓት ለቦረና ህዝብ ከዴሞክራሲም በላይ ነው የሚለው ፅሁፉ የአንድነቱ፣ የማንነቱ እና የባህሉ መገለጫ መሆኑን ያነሳል።

ቢቢሲ በበኩሉ የቦረና ማህረሰብ ዘመናትን የተሻገረ የዴሞክራሲ ክብረበዓል አክብሯል ሲል ዘግቧል።

ሥርዓቱ የዳበረ ባህላዊ አስተዳደር መገለጫ መሆኑንም ይገልፃል።

አስተዳደሩ የተቆረጠለት የሥልጣን ዘመን ያለው ሲሆን የአንድ አባ ገዳ የሥልጣን ዘመን 8 ዓመት ብቻ ነው ይላል።

ታዲያ 8 ዓመት ጠብቆ ለአዲስ አስተዳደር ቦታ መልቀቅ ክፍለ ዘመን የተሻገረ ዴሞክራሲን አመላካች ነው ብሏል።

መገናኛ ብዙሃኑ በሥርዓቱ አልፎ ቀጣይ የአባ ገዳነት መንበር የሚረከብ ወጣት ከልጅነቱ ጀምሮ በሥነ ምግባር እየተኮተኮተ በተግባር የተፈተኑ ሥልጠናዎችን ማለፍ እንደሚጠበቅበትም በዘገባቸው አመልክተዋል።

ይህም በቀጣይ የሥልጣን ዘመን የሚያገለግለውን ህዝብ ተረድቶ ሃላፊነቱን በተገቢው መንገድ እንዲወጣ ያግዘዋል ብለዋል።

በስምንት ዓመት አንድ ጊዜ የሚካሄደው የቦረና አባ ገዳ ሥልጣን ርክክብ ሥርዓት ለአንድ ሳምንት ያህል የሚቆይ ነው ።

በዚህ ጊዜ ውስጥ የተለያዩ የማህበረሰቡ የባህል እሴቶች ጎልተው እንደሚንፀባረቁ የዘገቡት ደግሞ ኢስት አፍሪካን ኼራልድ፣ ዘ ስታር እና ጋና ኒውስ ናቸው።

የወጣት ወንዶች፣ ያገቡ እና ያላገቡ ልጃገረዶች ድንቅ አለባበስንም ሳያደንቁ አላለፉም።

ግጭት በመፍታት እና ሠላምን በማውረድ የሚታወቀውን የሀደ ሲንቄዎች ሚናም የውጭ መገናኛ ብዙሃን ሽፋን የሰጡት ጉዳይ ነበር።

72ኛ የቦረና አባ ገዳ የስልጣን ርክክብ ሥርዓት (ባሊ) በተካሄደበት ወቅትም ከኬኒያ እና ከሀገር ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አንጋፋው የዴሞክራሲ ስርዓት ሲከናወን ለመታደም ችለዋል።

በማሬ ቃጦ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review