38ኛዉ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት የእውቅና እና የምስጋና መርሃ-ግብር ተካሄደ

You are currently viewing 38ኛዉ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት የእውቅና እና የምስጋና መርሃ-ግብር ተካሄደ

AMN-መጋቢት 5/2017 ዓ.ም

የአፍሪካ ህብረት 38ኛዉ የመሪዎች ጉባኤ እና የ46ኛው መደበኛ የአስፈጻሚ ም/ቤት ስብሰባ በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት የእዉቅና እና የምስጋና መርሃ-ግብር ተካሄዷል።

በስነ-ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ ኢትዮጵያ አዲስ አበባ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ መዲና መሆኗን ያሳየችበት ጉባዔ ነበር ብለዋል።

ጉባዔው የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ስኬት እና የኢኮኖሚ ማሻሻያ ውጤቶች ጎልቶ የታየበት እንደነበር ሚኒስትሩ ገልጸዋል። የዘንድሮው ጉባዔ ኢትዮጵያ በፓን አፍሪካ ንቅናቄ ልዩ ቦታ የያዘች መሆኗን ያረጋገጠችበት ነው ብለዋል።

ዶ/ር ጌዲዮን ጉባዔው የተሳካ እንዲሆን ለተሳተፉ የብሔራዊ ኮሚቴ አባላት እና በጎ ፍቃድ አገልግሎት ሰጪ ወጣት ካዴቶች ምስጋና አቅርበዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖም ለብሔራዊ ኮሚቴው፣በንዑስ ኮሚቴዎች ለተሳተፉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዲፕሎማቶች እና ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪ ወጣት ካዴቶች ምስጋና ችረዋል።

አምባሳደር ብርቱካን የተለያዩ ተቋማት እና ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በቁርጠኝነት እና በትጋት በመንቀሳቀሳቸው 38ኛው መሪዎች ጉባዔ በስኬት እንዲጠናቀቅ ማድረጉን በመግለጽ ጉባኤው ኢትዮጵያ በሁሉም መስኮች ያስመዘገበቻቸው ስኬቶች ደምቀው የወጡበት መሆኑን ተናግረዋል።

በስካይላይት ሆቴል በተደረገው የእውቅና ፕሮግራም እና የእራት ግብዣ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ፣የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታዎች አምባሳደር ብርቱካን አያኖ እና አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ለብሔራዊ ኮሚቴው እና ንዑስ ኮሚቴ ፣ጉልህ ሚና ላበረከቱ ግለሰቦች እና ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪ ወጣቶች የእውቅና ሰርተፍኬት ማበርከታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review