ከቆመ ተሽከርካሪ ላይ የጎን መስታወት (ስፖኪዮ) የሰረቀ ግለሰብ በ4 ዓመት ፅኑ እስራት ተቀጣ

You are currently viewing ከቆመ ተሽከርካሪ ላይ የጎን መስታወት (ስፖኪዮ) የሰረቀ ግለሰብ በ4 ዓመት ፅኑ እስራት ተቀጣ

AMN – መጋቢት 6/2017 ዓ.ም

ከቆመ ተሽከርካሪ ላይ የጎን መስታወት (ስፖኪዮ) የሰረቀ ግለሰብን በቁጥጥር ስር በማዋል በ4 ዓመት ፅኑ እስራት ማስቀጣቱን የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ገልጿል፡፡

ተከሳሽ ሀድራ ፈድሉ መሀመድ ወንጀሉን የፈፀመው የካቲት 28 ቀን 2017 ዓ.ም በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ልዩ ቦታው ሞቢል ዓለም ቡና ጀርባ ከቀኑ 8፡20 ሰዓት አካባቢ ነው፡፡

የግል ተበዳይ ተሽከርካሪያቸውን በመኖሪያ ቤታቸው አካባቢ አቁመው ሳለ ተከሳሽ በቦታው ላይ መንገደኛ በመምሰል የሰው መኖር አለኖሩን ካረጋገጠ በኋላ ግምቱ 20ሺህ የሆነ ከሰሌዳ ቁጥር ኮድ 2 ሲ 51586 አ/አ ቼሪ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ላይ የጎን መስታወት (ስፖኪዮ) ገንጥሎ ከአካባቢው ሊሰወር ችሏል፡፡

የወንጀሉ መፈፀም ሪፖርት የደረሰው የአውጉስታ ፖሊስ ጣቢያ ከአካባቢው ላይ በሰበሰበው መረጃ እና የካሜራ ቅጂ አማካኝነት ተከሳሹን በመለየት ባደረገው ክትትል ወንጀሉ በተፈፀመ በ4 ቀናት ውስጥ በቁጥጥር ስር ሊያውለው መቻሉን የጣቢያው የወንጀል ምርመራ ማስተባበሪያ ኃላፊ ኢንስፔክተር አክሊሉ በላቸው ገልፀዋል፡፡

ፖሊስ ተገቢውን ማስረጃ በማሰባሰብና የወንጀል ምርመራ መዝገቡን ለዐቃቤ ህግ በማቅረብ ክስ እንዲመሰረትበት ማድረጉን የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡

በተከሳሽ ላይ የተደራጀውን የወንጀል ምርመራ ክስ ሲከታተል የቆየው በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ኮልፌ ምድብ 1ኛ ወንጀል ፈጣን ችሎት መጋቢት 4 ቀን 2017 ዓ/ም በዋለው ችሎት ተከሳሽን ያርማል ሌሎች ወንጀል ፈፃሚዎችን ያስጠነቅቃል በማለት ተከሳሽ ፈድሉ መሀመድን በ4 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኖበታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review