AMN – መጋቢት 7/2017 ዓ.ም
“በእርዳታ ሀገር አያድግም፤ እርዳታን እንደ ዕድል በመጠቀም ከተረጂነት ነጻ መውጣት አለብን” ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር ዓባይ ገለጹ፡፡
ቀጥታ ድጋፍ እና በአካባቢ ልማት የከተማ ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም 3ኛ ዙር ማስጀመሪያ ሥነ-ስርአት በየካ ክፍለ ከተማ ተካሂዷል፡፡
የከተማ ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም ዜጎችን ወደ ቋሚ የስራ ዕድል ተጠቃሚነተ ለመግባት የሚያግዝ ዕድል በመሆኑ በቀጣይ 3 አመታት ውስጥ ከሚገኘው ገቢ ላይ 20 በመቶ በመቆጠብ ወደ ቋሚ ገቢ የሚያስገኝ ስራ መሰማራት እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር ዓባይ ገልጸዋል።

አዲስ አበባ ከተማ በአንደኛ እና በሁለተኛ ዙር የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ተጠቃሚ ዜጎችን ወደ ቋሚ የስራ ዕድል በማስገባት ተሞክሮ መሆን የሚችል ስራ መስራት መቻሏንም ገልጸዋል።
በ3ኛው ዙር በክፍለ ከተማው በቀጥታ ድጋፍ እና በአካባቢ ልማት ከ8 ሺህ በላይ ዜጎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የየካ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ብርሃኑ ገልጸዋል።
በማስጀመር መርሃ ግብሩ ላይ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ሥራ እና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥራቱ በየነ እና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።
በዳንኤል መላኩ