AMN – መጋቢት 7/2017 ዓ.ም
የቂርቆስ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ከ6 ሺ 377 በላይ ነዋሪዎች በከተማ የአካባቢ ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም ተጠቃሚ የሚያደርግ መርሃ ግብር አካሂዷል፡፡
መርሐ ግብሩ በስራና ክህሎት ጽኅፈት ቤት የተመራ ሲሆን፣ በክፍለ ከተማው ባለፉት ዓመታት ከ45 ሺህ በላይ ነዋሪዎች በፕሮግራሙ ተጠቃሚ መሆናቸው ተገልጿል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር አዲሱ ሻንቆ፣ ተጠቃሚ የሚሆኑት የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በመንግስት ድጋፍ በሚተገበረው የከተማ ልማታዊ ሴፍትኔት መሆኑን ገልጸው፣ የእድሉ ተጠቃሚ የሆናችሁ ነዋሪዎችም ተግታችሁ በመስራት እራሳችሁን እንድትቀይሩ ሲሉ አሳስበዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መስሪያ ቦታዎች አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ታረቀኝ ወርቅነህ በበኩላቸው፣ በዛሬው እለት ወደ ስራ የገባችሁ ተጠቃሚዎች በተመረጡ 5 ፕሮግራሞች ላይ ተሰማርታችሁ ጠንክራችሁ በመስራት እራሳችሁን ከተረጅነት ወደ ምርታማነት ልትቀይሩ ይገባል ማለታቸውን ከክፍለ ከተማው ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡