AMN – መጋቢት 8/2017 ዓ.ም
የ2024/25 የእንግሊዝ ካራባኦ ዋንጫ ትናንት ምሽት ፍጻሜውን አግኝቷል፡፡
ኒውካስትል አርሰናልን ሊቨርፑል ቶትንሃምን አሸንፈው ነበር ለግዙፉ የዌምብሌ ስታድዬም የፍጻሜ ጨዋታ የደረሱት፡፡
ኒውካስትል 2ለ1 አሸንፎ ከ70 ዓመታት በኋላ የሀገር ውስጥ ዋንጫን አንስቷል፡፡
በ1955 ማንችስተር ሲቲን 3ለ1 አሸንፎ የኤፍ ኤ ዋንጫን ካነሳ ወዲህ ምንም ዓይነት ዋንጫ ለማንሳት ያልታደለው ኒውካስትል፣ ምስጋና ለዳን በርን እና አሌክዛንደር ይሳቅ ካራባኦ ዋንጫን አንስቷል፡፡
የመክፈቻዋን ግብ ያስቆጠረው ደግሞ አምበሉ ዳን በርን ነው፡፡
በመጪው ግንቦት ወር መጀመሪያ 33 ዓመት የሚሞላው ዳን በርን 2 ሜትር ከ01 ሳንቲ ሜትር ስለሚረዝም ከሁሉም ተጨዋቾች ጎልቶ ይታያል፡፡
የበርሚንግሃም፣ ዊጋን አትሌቲክ እና ብራይተን የቀድሞ ተከላካይ ዳን በርን ለእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ጥሪ ደርሶት አያውቅም፡፡
ዘንድሮ ግን የሶስቱ አናብስት አሰልጣኝ ቶማስ ቱኼል የቁመተ መለሎው ተከላካይ ብቃት አሳምኗቸዋል፡፡
ጀርመናዊ አሰልጣኝ ከአልባኒያና ላቲቪያ ጋር ላሉባቸው ሁለት የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ተጨዋቾችን ሲጠሩ ለመጀመሪያ ጊዜ ዳን በርንን አካተዋል፡፡
በ33ኛ ዓመት ልደቱ ዋዜማ አርብ ምሽት ለብሔራዊ ቡድን ጥሪ የደረሰው ዳን በርን ትናንት ምሽት በወሳኙ የዌምብሌ ጨዋታ ግብ አስቆጥሮ የቱኼልን ውሳኔ ትክክኛንት በተግባር አስመስክሯል፡፡
ግብ ከማስቆጠር ባለፈ የቡድኑን የመከላከል ሚዛን ሲያስጠብቅ ያመሸው በርን፣ ማግፒዎቹን ከ70 ዓመታት በኋላ ከዋንጫ ጋር አስታርቋል፡፡
ከኤርትራውያን ቤተሰቦች የተገኘው አሌክዛንደር ይሳቅ ሁለተኛዋን የኒውካስትል ዩናይትድ ግብ ያስቆጠረ ተጨዋች ነው፡፡
ይሳቅ በውድድር ዓመቱ ያስቆጠራቸውን አጠቃላይ ግቦች 23 አድርሷል፡፡
በፌድሪኮ ቺየሳ የማስተዛዘኛ ግቡን ያገኘው ሊቨርፑል በበኩሉ በአንድ ሳምንት ውስጥ ከሁለት ዋንጫ ውጭ ሆኗል፡፡
በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ማክሰኞ ምሽት በመለያ ምት በፒ ኤስጂ ተሸንፎ ከመድረኩ የተሰናበተው የመርሲሳይዱ ክለብ ትናንት ምሽት ደግሞ በካራበኦ ዋንጫ ፍጻሜ በኒውካስትል ተሸንፎ ሁለተኛ ሆኖ አጠናቋል፡፡
በታምራት አበራ