በውድድር ዓመቱ 133 ግቦችን ተጋጣሚ ላይ ያስቆጠረው ባርሴሎና

You are currently viewing በውድድር ዓመቱ 133 ግቦችን ተጋጣሚ ላይ ያስቆጠረው ባርሴሎና

AMN-መጋቢት 08/2017 ዓ.ም

ባርሴሎና ጀርመናዊ ሃንሲ ፍሊክን ከሾመ በኋላ አዳዲስ ክብረ ወሰኖችን እያስመዘገበ ጉዞውን ቀጥሏል፡፡ በ2024/25 የውድድር ዓመት የካታሎኑ ክለብ ገና የውድድር ዓመቱ ሳይጠናቀቅ 133 ግቦችን ተጋጣሚዎቹ ላይ አስቆጥሯል፡፡

በላሊጋው ብቻ 70 ግቦችን በተጋጣሚ መረብ ላይ ያሳረፈው ባርሳ፣ ከሪያል ማድሪድ 16 ከአትሌቲኮ ማድሪድ 29 የበለጡ ግቦችን አስቆጥሯል፡፡

በላሊጋው 28ኛ ሳምንት ተጠባቂ ጨዋታ ትናንት ምሽት ባርሴሎና አትሌቲኮ ማድሪድን 4ለ2 አሸንፏል፡፡ አትሌቲኮ እስከ 72ኛው ደቂቃ 2ለ0 ሲመራ አምሽቶ ነበር፡፡ ነገር ግን በ28 ደቂቃ ውስጥ አራት ግቦችን ያስቆጠረው የካታሎኑ ክለብ ድሉን ነጥቆታል፡፡

ዡሊያን አልቫሬስና አሌክዛንደር ሶርሎት ባስቆጠሯቸው ግቦች አትሌቲኮ እስከ 72ኛው ደቂቃ 2ለ0 ሲመራ አመሸ፡፡ ይሁን እንጂ ሮበርት ሎዋንዶውስኪ በ72ኛው፣ ተቀይሮ የገባው ፌራን ቶሬስ በ78ኛውና እና 98ኛው እንዲሁም ላሚን ያማል በ92ኛው ደቂቃ አከታትለው ያስቆጠሯቸው ግቦች የካታሎኑን ክለብ ባለ ድል አድርገዋል፡፡

‹‹ባርሴሎና ምርጥ ጨዋታ የሚጫወት ቡድን ነው›› ብለዋል የአትሌቲኮ ማድሪዱ አሰልጣኝ ዲየጎ ሲሞኒ፡፡ የሃንሲ ፍሊኩ ስብስብ በ2025 ብቻ 60 ግቦችን ተጋጣሚ ቡድን መረብ ላይ አሳርፏል፡፡ በ2025 በአውሮፓ አምስት ታላላቅ ሊጎች ያልተሸነፈው ብቸኛ ክለብም ባርሴሎና ነው፡፡

በሐኪሙ ድንገተኛ ህልፈት ምክንያት ከኦሳሱና ጋር ያደርግ የነበረውን ጨዋታ ያራዘመው ባርሴሎና ትናንት በማሸነፉ ነጥቡን 60 አድርሶ የደረጃ ሰንጠረዡን መሪነት አስመልሷል፡፡

ከባርሴሎና የበለጠ አንድ ጨዋታ ያደረገው ሪያል ማድሪድ በ60 ነጥብ በርስ በርስ ግንኙነት አንሶ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ አትሌቲኮ ማድሪድ በበኩሉ በ56 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል፡፡

በሌሎች ውጤቶች ኦሳሱና በሄታፌ 2ለ1 ሲሸነፍ፣ ሪያል ቤትስ በሌጋኔስ 2ለ0 ሲመራ አምሽቶ 3ለ2 አሸንፏል፡፡ ሲቪያ በአትሌቲክ ቢልባኦ 1ለ0 ሲረታ፣ ራዮ ቫልካኖ እና ሪያል ሶሴዳድ በበኩላቸው 2ለ2 ተለያይተዋል፡፡

በታምራት አበራ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review