AMN-መጋቢት 9/2017 ዓ.ም
የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በኢትዮጵያ የአየርላንድ አምባሳደር ኦሊቪያ ሌስሊ ጋር በጤና ጉዳዮች እና አጋርነት ላይ ተወያይተዋል፡፡
አየርላንድ ባለፉት ዓመታት የተለያዩ ዓለም አቀፍ የጤና ውጥኖችን ለመተግበር ኢትዮጵያን እየረዳች መሆኑን የጠቆሙት የጤና ሚኒስትሯ፣ አየርላንድ ለኢትዮጵያ ላደረገችው የረጅም ጊዜ ድጋፍ አመስግነዋል።
የጤና አገልግሎት አቅርቦት ሰንሰለትን ማሻሻል፣ በኢትዮጵያ ያለውን የጤና አጠባበቅ የሰው ኃይል ማጠናከር፣ በሽታዎችን ለመከላከል እና የህዝብ ጤናን ለማሻሻል የሚረዱ መንገዶች እና ስርዓተ-ምግብ ላይ ተወያይተዋል።
በተጨማሪም ዘላቂ ልማት ግቦች፣ የክትባት አቅርቦት እና የማህበረሰብ አቀፍ ኢንሹራንስ እንዲሁም አጠቃላይ የጤና ስርዓትን ከማጠናከር አኳያም መክረዋል።
አምባሳደር ኦሊቪያ ኢትዮጵያ እና አየርላንድ ሊተባበሩባቸው የሚችሉባቸው በርካታ ዘርፎች እንዳሉ ጠቅሰው፣ ትብብሩ በኢትዮጵያ የተሻለ የጤና አገልግሎት፣ የተሻለ የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት እና ጠንካራ የበሽታ መከላከል ስልቶችን ለማምጣት ያስችላል ብለዋል።
አየርላንድ የኢትዮጵያን የጤና ዘርፍ ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኗን አምባሳደሯ መግለፃቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።