AMN-መጋቢት 9/2017 ዓ.ም
የ2017 በጀት ዓመት ሀገር አቀፍ የክትባት መርሐ-ግብር አፈጻጸም እና በክትባት የምንከላከላቸው በሽታዎች ቅኝት ሪፖርት የግምገማ መድረክ ተካሂዷል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ድጉማ፣ የክትባት ፕሮግራም በሀገራችን ላለፉት አራት አሰርት ዓመታት ሰፋፊ ስራዎች የተሠራበት፣ የወደፊት ሀገር ተረካቢ ህጻናት ሞት እንዲቀንስ እና በአግባቡ እንዲያድጉ ያስቻለ፣ ከጤና ባሻገር ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ተጠቃሚ ያደረገ ጠንካራ ፕሮግራም ነው ብለዋል።
ጤና ሚኒስቴር ከኢትዮጰያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ጋር በመሆን በክትባት ላይ በቅንጅት እየተሰራ እንዳለ እና በርካታ ውጤት እየተገኘ መሆኑንም ዶክተር ደረጀ ገልጸዋል።
በተለይ ከሰባት ሚሊየን በላይ ልጃገረዶች የኤች ፒ ቪ ክትባት እንዲያገኙ መደረጉ ትልቅ ስኬት መሆኑን በንግግራቸው ያነሱ ሲሆን፣ የሄፒታይተስ፣ የሚዝል እና የወባ ክትባቶችን ለመስጠት ጥረት እየተደረገ እንዳለም ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ በተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ክስተቶች ሳቢያ ክትባት ተዳራሽ ያልሆኑ እና ክትባት ጀምረው ያቋረጡትን ተደራሽ ለማድረግ ስርዓት ተዘርግቶ በተለይ የመጀመሪያ አሀድ ጤና ክብካቤ ላይ በትኩረት በመስራት ወረርሽኞችን መመከት እንዲቻል አቅጣጫ መስጠታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።