AMN-መጋቢት 9/2017 ዓ.ም
ለዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ድርድር ስዊዘርላንድ ጄኔቫ የሚገኘው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ከአሜሪካ ልዑካን ቡድን ጋር በሁለትዮሽ የገበያ መዳረሻ ድርድር ዙሪያ ዛሬ ከሰዓት ሰፊ ውይይት ማድረጉን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ ለዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ድርድር ስዊዘርላንድ ጄኔቫ የሚገኘው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በሁለተኛ ቀን ቆይታው ከአሜሪካ ልዑካን ቡድን ጋር በሁለትዮሽ የገበያ መዳረሻ ድርድር ዙሪያ ተወያይቷል፡፡
የገበያ ዕድሎችን ከማስፋት አንፃር በአገልግሎት፣ በግብርና እና ሌሎች ምርቶች የገበያ ዕድል ዙሪያ ከአሜሪካ ለተነሱ ጥያቄዎች ተገቢውን ማብራሪያ እና ምላሽ መሰጠቱንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
ወደፊትም የሁለቱ ሀገራት የንግድ ግንኙነት መርህ ተኮር ሆኖ በሚጠናከርበት አግባብ ላይ የጋራ ግንዛቤ መፈጠሩንም አንስተዋል፡፡