ሩሲያ እና ዩክሬን የአየር ጥቃት ተሰነዛዘሩ

You are currently viewing ሩሲያ እና ዩክሬን የአየር ጥቃት ተሰነዛዘሩ

AMN – መጋቢት 10/2017 ዓ.ም

ሩሲያ እና ዩክሬን አንዳቸው የአንዳቸውን መሰረተ ልማቶች የሚያወድም የአየር ጥቃት መሰነዛዘራቸው ተገልጿል፡፡

የአየር ጥቃቱ የተፈጸመው የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቪላድሚር ፑቲን ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት ሩሲያ የዩክሬንን የኃይል መሰረተ ልማቶች ዒላማ ያደረገ ጥቃት እንደምታቆም ከተናገሩ ከሰዓታት በኋላ መሆኑ ተነግሯል፡፡

የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ፣ ሩሲያ የሰነዘረችው የአየር ጥቃት ሆስፒታሎችንም ያካተተ እንደነበር አመልክተዋል፡፡

ዜለንስኪ አያይዘውም የሩሲያው ፕሬዚዳንት ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጋር በነበራቸው ውይይት፣ የቀረበላቸውን የተኩስ አቁም ስምምነት እንደማይቀበሉ መግለፃቸውን አንስተዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ቪላድሚር ፑቲን በበኩላቸው፣ ሙሉ ለሙሉ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ የዩክሬን አጋሮች ለዩክሬን የሚያደርጉትን ወታደራዊ ድጋፍ ሲያቆሙ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ ይህንን ቅድመ ሁኔታ የዩክሬን አጋሮች ከዚህ ቀደም እንደማይቀበሉ መግለፃቸው ይታወሳል፡፡

በደቡባዊ ሩሲያ ክራስኖዳር ክልል የሚገኙ ባለ ሥልጣናት የዩክሬን የአየር ጥቃት በአንድ የነዳጅ ማከማቻ ላይ አነስተኛ እሳት እንዳስነሳ መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review