AMN – መጋቢት 10/2017 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ “የወል ትርክት” በሚል ርዕስ አባ ሳሙኤል በሚገኘው ማረሚያ ቤት ውስጥ ለሚገኙ የህግ ታራሚዎች አሳታፊ ቴአትር አካሂዷል።
በማረሚያ ቤት ውስጥ የሚገኙ የህግ ታራሚዎች በሥነ- ምግባር እንዲታነፁ እና የኪነ ጥበብ ፍቅር እንዲኖራቸው በህፃናትና ወጣቶች ቴአትር ቤት የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች አሳታፊ ቴአትር ስራ ቀርቧል።
የቀረበው የኪነ ጥበብ ስራ የህግ ታራሚዎች በእርማት ጊዜያቸው የተለያዩ ስራዎችን ለምደው ወደ ማሕበረሰቡ ሲቀላቀሉ አምራች ዜጋ በመሆን ከራሳቸው አልፈው ማሕበረሰቡን እንዲያገለግሉ የሚያስተምር አሳታፊ ቴአትር መሆኑ ተገልጿል።
ቢሮው ለኪነ ጥበብ ዘርፍ ትኩረት በመስጠት በየክ/ከተማው በሚገኙ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች፣ ማረሚያ ቤቶችና በሌሎች ተቋማት እየተዘዋወረ የኪነ ጥበብ ስራዎችን እያቀረበ ህብረተሰቡን በማዝናናት ላይ እንደሚገኝ ከአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል፡፡