AMN-መጋቢት 10/2017 ዓ.ም
“5ኛው የሀገራችን የአለም ንግድ ድርጅት የስራ ቡድን ስብሰባ በስኬት መጠናቀቁን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለፁ።
በተለያዩ የድርድር ነጥቦች ዙሪያ ከ110 በላይ ጥያቄዎችን በመቀበል ውጤታማ ድርድር ያካሄደው የድርድር ቡድኑ ዛሬ ማምሻውን ድርድሩን ማጠናቀቁን ሚኒስትሩ በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ ገልፀዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም “የሚቀጥለው 6ኛው የስራ ቡድን ስብሰባ በያዝነው ዓመት ወርሃ-ሃምሌ እንዲካሄድ በመስማማት ኢትዮጵያ በ2018 ካሜሩን በሚካሄደው 14ኛው የአለም ንግድ ሚኒስትሮች ስብሰባ የአለም ንግድ ቤተሰብ እንድትቀላቀል ሁላችንም የራሳችንን የቤት ስራ ለመስራት ተስማምተን ማምሻውን ድርድራችንን ቋጭተናል” ብለዋል።
በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ቀሪ የሁለትዮሽ ድርድሮችን እና ከፅ/ቤቱ ጋር ውይይቶች እንደሚኖሩም ሚኒስትሩ ገልፀዋል።