AMN-መጋቢት 11/2017 ዓ.ም
በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም 61 በመቶ መድረሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በዚህም ኢንዱስትሪን በተመለከተ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ስትሪንግ ኮሚቴ ተቋቁሞ በኢንዱስትሪ ዘርፉ ላይ ያሉ ማነቆዎችን የመፍታት ስራ ሲከናወን መቆየቱን አንስተዋል።
ይህንንም ተከትሎ የውጭ ምንዛሬ፣ የኃይል አቅርቦት እና ሌሎች ችግሮች የተለዩ ሲሆን፣ ችግሮቹን ለመቅረፍም እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ለአብነትም በዘንድሮው ዓመት ብቻ ለኢንዱስትሪ ዘርፉ የቀረበው የኃይል አቅርቦት ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጻር የ50 በመቶ ብልጫ እንዳለው አመልክተዋል።
ከጥቂት ዓመታት በፊት የአቅርቦት ጥያቄ የነበረበት የሲሚንቶ ምርትም፣ አሁን ላይ ለውጭ ገበያ ጭምር ማቅረብ የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ እንደሆነ ነው ገለጹት።
የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም 61 በመቶ የደረሰ ሲሆን፣ በዚህ ዓመት ብቻ 55 አዳዲስ ፋብሪካዎች ስራ መጀመራቸውንም አመላክተዋል።