AMN – መጋቢት 11/2017 ዓ.ም
ዛሬ መጋቢት 11 ቀን 2017 ዓ.ም ከቀኑ 9:46 ሰዓት ላይ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ -ከተማ ወረዳ 15 ሀጫሉ ጎዳና አካባቢ በኖክ ነዳጅ ማደያ ላይ ተከስቶ የነበረዉ የእሳት አደጋ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ መቆጣጠር መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ የእሳትና የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የእሳት አደጋዉ ያጋጠመዉ በማደያዉ ነዳጅ በመቅዳት ላይ የነበረ ዳማስ ተሽከርካሪ ተገቢዉን የደህንነት መስፈርት ሳይጠብቅ የተሽከርካሪዉን ሞተር በማስነሳቱ መሆኑን የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት አቶ ንጋቱ ማሞ አስታዉቀዋል፡፡
የእሳት አደጋዉ እንደተከሰተ በኮሚሽኑ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ቅርንጫፍ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች በቦታዉ በፍጥነት በመድረስ ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ እሳቱ ሳይስፋፋ መቆጣጠር ችለዋል።
በእሳት አደጋዉ በአንድ ዳማስ ተሽከርካሪ እና በነዳጅ መቅጃው ማሽን ላይ መጠነኛ ጉዳት ከማጋጠሙ ዉጪ የደረሰ ጉዳት የለም ብሏል ኮሚሽኑ፡፡
በነዳጅ ማደያ ውስጥ ለእሳት አደጋ አጋላጭ ሁኔታዎች በርካታ በመሆናቸዉ አሽከርካሪዎች ነዳጅ ለመቅዳት ወደ ነዳጅ ማደያ በሚገቡበት ጊዜ የአደጋ ደህንነት መስፈርትን ጠብቀዉ እንዲቀዱ የነዳጅ መሸጫ ድርጅት ሰራተኞችም አስፈላጊዉን ቁጥጥር እንዲያደርጉ ኮሚሽኑ አሳስቧል፡፡
በሸዋዬ ከፍያለው