AMN-መጋቢት 12/2017 ዓ.ም
ለ2017 የአረንጓዴ አሻራ መርሀ-ግብር እስካሁን 4 ነጥብ 7 ቢሊየን ችግኞች መዘጋጀታቸውን የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገለጹ።
14ኛው ዓለም አቀፍ የደን ቀን “ደንና ምግብ” በሚል መሪ ሀሳብ እየተከበረ ነው።
በመርሀ-ግብሩ የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ(ዶ/ር)፣ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ሙባረክ ኤልያስ፣ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ እያሱ ኤልያስ (ፕ/ር)፣ የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር ከበደ ይማም እንዲሁም የፌደራል እና የክልል የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በመርሐ-ግብሩ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ በመሬት አቀማመጥ፣ በተፈጥሮ ሀብት እንዲሁም ተስማሚ የአየር ንብረት የታደለች ሀገር መሆኗን አስገንዝበዋል።
በብዝኃ ህይወት ስብጥርም በዓለም ተጠቃሽ ከሆኑ ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗን ጠቁመዋል።
ደን ዘላቂ ምርታማነትን ለማረጋገጥ የማይተካ አስተዋጽኦ እንዳለው አመላክተዋል።
ከዚህ ቀደም በነበሩ ጊዜያት ደንን መሰረት ባላደረገ የኢኮኖሚ ዘይቤ ምክንያት የከፋ የደን መመናመን እንደነበር አስታውሰዋል።
አሁን ላይ ኢትዮጵያ ይህንን የሚያስተካክል ፖሊሲ ቀርጻ በመተግበር ላይ እንደምትገኝ ነው የገለጹት።
በተጨማሪም ከምግብ ፍጆታ ባለፈ ለውጭ ገበያ በማቅረብ የኢኮኖሚ ምንጭ መሆኑን እና በስራ እድል ፈጠራም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቁመዋል።
ለ2017 የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር እስካሁን 4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ችግኞች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
መንግስት ከየትኛውም ጊዜ በላይ ለተፈጥሮ ጥበቃ እና ለአረንጓዴ ልማት ልዩ ትኩረት እንደሰጠ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።