ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 21 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ድጋፍ ተደርጓል

You are currently viewing ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 21 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ድጋፍ ተደርጓል

AMN – መጋቢት 12/2017

ኢትዮጵያዊያን እስካሁን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 21 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የተባበረ ክንድ እየተገነባ ያለ ትልቅ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክት እንደሆነ ይታወቃል።

የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከግብ እንዲደርስ ዜጎች በገንዘባቸው ፣በእውቀታቸውና በጉልበታቸው አጋርነታቸውን በቁርጠኝነት እያሳዩ ይገኛሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ትናንት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ የግድቡ ግንባታ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቅ መናገራቸው ይታወቃል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) የህዳሴ ግድብ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ለአንድ ዓላማ ያሰለፈ ሀገር የምትኮራበት ግዙፍ ፕሮጀክት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በተለይም ህብረተሰቡ ለግድቡ ግንባታ የሚያደርጋቸው ዘርፈ ብዙ ድጋፎች ከድህነት ለመላቀቅና ለማደግ ያለውን ፍላጎት በተግባር ያሳየበት ነው ሲሉም አክለዋል።

ኢትዮጵያዊያን የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ አንስቶ እስካሁን ከ 21 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ህዝቡ በሀብት ከሚያደርገው እገዛ ባለፈ 120 ቢሊየን ብር የሚገመት የጉልበት አስተዋጽኦ ማበርከቱን አክለዋል።

ኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እድገቷን የሚያረጋግጡ ያልተነኩ እምቅ የተፈጥሮ ሀብቶች ያላት በመሆኑ ፀጋዎቿን ጥቅም ላይ ለማዋል የልማት ስራዎችን ቀርጸን መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

በቀጣይም የህዳሴ ግድቡ ግንባታ ከጫፍ እንዲደርስ ዜጎች ለፕሮጀክቱ እያደረጉት ያለውን የተለያዩ ድጋፎች አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ ማቅረባቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review