የመዲናችን ኪነ-ጥበባዊ መሰናዶዎች

You are currently viewing የመዲናችን ኪነ-ጥበባዊ መሰናዶዎች

ከሰሞኑ በመዲናችን የተለያዩ ኪነ-ጥበባዊ ስራዎች ለጥበብ አፍቃሪያን ደርሰዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል አዳዲስ የመጽሐፍት ምርቃትና ህትመት፣ የሥዕል ዓውደ-ርዕይ፣ ኪነ-ጥበባዊ ውይይቶች እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡ ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናትም መሰል የጥበብ ዝግጅቶች ተሰናድተዋል፡፡ የቴአትር መርሃ ግብር፣ የስዕል አውደ ርዕይ እና ሌሎች ከእነዚህ መካከል ይገኙበታል፡፡ ለመረጃ ይሆንዎት ዘንድ የአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍል መርሃ ግብሮቹን እንደሚከተለው አዘጋጅቷቸዋል፡፡


መጽሐፍት
የሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅን የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ በዛሬው እለት ተመርቆ ለንባብ ይበቃል፡፡ “ምጥቀት በቅኔ አክናፍ” የተሰኘው ይህ መጽሐፍ ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ጀምሮ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ መኮንን አዳራሽ ይመረቃል፡፡ በዕለቱም ከሎሬቱ ስራዎች ቅንጭብ ተውኔት፣ ግጥም፣ ሙያዊ ዳሰሳ እና ትዝታዎቻቸው ያጋራሉ ተብሏል፡፡
በሌላ የመጽሐፍ መረጃ  በሀገር ውስጥና በውጭው ዓለም በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በማስተማር የሚታወቁት ኃይሉ ሀብቱ (ዶ/ር) “AKSUM A glimpse into an African Civilization” የተሰኘ መጽሐፍ በዛሬው እለት ተመርቆ ለንባብ ይበቃል። በምርቃት መርሃ ግብሩ ላይ  ፕሮፌሰር ኤመሪተስ ሽብሩ ተድላ እና የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት (የወመዘክር) ዳይሬክተር ይኩኖአምላክ መዝገቡ በመጽሐፉ ዙሪያ ትንታኔ ይሰጣሉ፡፡ መጽሐፉ የሚመረቀው ወመዘክር ሲሆን ሰዓቱ ደግሞ 3፡30 እንደሆነ ተገልጿል፡


ሥዕል
“የደራሲው ስዕል” የተሰኘው የስዕል አውደ ርዕይ በእይታ ላይ ይገኛል፡፡ በሰዓሊ ምዕራፍ ግሩም የተሳሉ ስዕሎች የቀረቡበት ይህ አውደ-ርዕይ ሃያት ሬጀንሲ ሆቴል በሚገኘው ፈንድቃ  የባሕል ማዕከል  እስከ ፊታችን ሰኞ መጋቢት 15 ቀን 2017 ዓ.ም ለእይታ እንደሚቆይ ተገልጿል፡፡
በሌላ መረጃ ሰባት ወጣት ሰዓሊያን በጋራ ያዘጋጁት “ሪትም” የስዕል ዓውደ-ርዕይ በመታየት ላይ ነው፡፡ ከሳምንት በፊት በይፋ በተከፈተው በዚህ የሥዕል አውደ-ርዕይ ላይ ከተሳተፉት ወጣት ሰዓሊያን መካከል አለምሰገድ በሃይሉ፣ አሌክሳንደር ፍስሃዬ፣ ዳዊት ጎሳዬ፣ ማህሌት አፈወርቅ፣ ሳሙኤል እንዳለማው ይገኙበታል፡፡ ዓውደ-ርዕዩ መልከ-ብዙ ግለሰባዊና ማህበረሰባዊ ጭብጦችን የሚዳስሱ ስራዎች የቀረቡበት እና በላፍቶ ዘመናዊ የሥነ-ጥበብ ጋለሪ ውስጥ እየታየ ሲሆን እስከ መጋቢት 23 ቀን ድረስ ለተመልካቾች ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
የስነ-ጥበብ አውደ-ርዕይ


በታምራት ስልጣን የተዘጋጀው “Resonance of the Meketefiya” የስነ-ጥበብ አውደ-ርዕይ ባሳለፍነው ረቡዕ ለእይታ በቅቷል፡፡ የሴቶችን ጥንካሬ የሚያወሱ የጥበብ ስራዎች የቀረቡበት ይህ አውደ-ርዕይ ቦሌ፣ ብሪቲሽ ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት አጠገብ በሚገኘው አርታዊ ጋለሪ እየታየ ሲሆን  እስከ ፈረንጆቹ መጋቢት 23 ቀን ድረስ በእይታ ላይ ይቆያል፡፡
የቴአትር መርሃ ግብር
በመዲናችን አዲስ አበባ ቅዳሜ እና እሁድ ከሚታዩ ቴአትሮች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡ ባሎች እና ሚስቶች የተሰኘው ቴአትር ቅዳሜ 8:00 ሰዓት፣ ባቡሩ የተሰኘው ቴአትር ደግሞ 11፡30 ሰዓት  በብሔራዊ ቴአትር ይታያሉ። እሁድ ሸምጋይ ሸምጋይ ቴአትር በ8፡00 ሰዓት ለእይታ የሚቀርብ ሲሆን እምዩ ብረቷ የተሰኘው ቴአትር ደግሞ በብሔራዊ ቴአትር 11፡30 ሰዓት ላይ ይታያል፡፡ በቀጣይ ቀናት  ሐሙስ ቀን 11:30 ሰዓት ደግሞ ጎዶ’ን ጥበቃ በብሔራዊ ቴአትር፣  አርብ በ12፡00 ሰዓት ዋዋጎ በዓለም ሲኒማ፣ አርብ በ11፡30 ሰዓት የሕይወት ታሪክ በብሔራዊ ቴአትር ለጥበብ አፍቃሪያን ለዕይታ ይቀርባሉ፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review