50 በመቶው የወጪና የገቢ ጭነት በባቡር ይጓጓዛል – የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር

You are currently viewing 50 በመቶው የወጪና የገቢ ጭነት በባቡር ይጓጓዛል – የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር

AMN – መጋቢት 13/2017 ዓ.ም

የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር አክሲዮን ማህበር 50 በመቶ የሚሆነውን የኢትዮጵያን የወጪና የገቢ ጭነት ለመሸፈን አቅዶ እየሰራ መሆኑን የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር አስታወቀ።

አክሲዮን ማህበሩ እቃዎችን በባቡር የማጓጓዝ አቅሙን በየዓመቱ በ14 ነጥብ 2 በመቶ እያሳደገ እንደመጣም ተገልጿል፡፡

ወደ ውጭ ከተላከው ቡና 98 በመቶ የሚሆነው በባቡር የተጓጓዘ ሲሆን ማዳበሪያን ጨምሮ የመልቲ ሞዳልና ዩኒ ሞዳል ኮንቲነር ጭነቶችን፣ የቁም እንስሳትን፣ ከባድ ማሽኖችን፣ አውቶቡሶችና አዳዲስ የጭነት ተሽከርካሪዎችን እያጓጓዘ እንደሚገኝም ተመላክቷል፡፡

የሚበላሹ ጭነቶችን በኮንቴነር አሽጎ በማጓጓዝ ጥራታቸውን እንደጠበቁ ለውጪ ገበያ በማቅረብ ከውጭ ንግዱ ሊገኝ የሚታሰበውን ገቢ በማስጠበቅ በኩል ሚናውን እየተወጣ እንደሚገኝም ሚኒስቴሩ ገልጿል።

የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር አክሲዮን ማህበር የኢትዮጵያን ወጪ ገቢ ጭነት 50 በመቶ የሚሆነውን ለመሸፈን፣ በየቀኑ 14 ባቡሮችን በማሰማራት አገልግሎት በመስጠት፣ የጭነት ባቡር ጉዞ ፍጥነትን በሰዓት ወደ 58 ኪሎ ሜትር ለማድረስ እንዲሁም በባቡር የሚሰጠውን አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ዲጂታሊዝ ለማድረግ አቅዶ እየሰራ መሆኑም ተመላክቷል፡፡

የመልቲ ሞዳልና የጭነት ማስተላለፍ ስራ ላይ የተሟላ አገልግሎት ለመስጠትም በቂ ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ እና በቅርቡ የመልቲ ሞዳል አከናዋኝነት ንግድ ስራ ፈቃድ እና የእቃ አስተላላፊነት የብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ማግኘቱን ከትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review