ፓርላማው የህጻናትን ሁለንተናዊ መብቶችና ጥቅሞች ለማረጋገጥ አዎንታዊ አስተዋጽኦ አለው

You are currently viewing ፓርላማው የህጻናትን ሁለንተናዊ መብቶችና ጥቅሞች ለማረጋገጥ አዎንታዊ አስተዋጽኦ አለው

AMN- መጋቢት 14/2017 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዘይነባ ሽኩር፣ የህጻናት ፓርላማ የህጻናትን ሁለንተናዊ መብቶችና ጥቅሞች እንዲረጋገጡ አዎንታዊ አስተዋጽኦ አለው ሲሉ ገለጹ።

በአዲስ አበባ የተማሪዎች የህጻናት ፓርላማ በይፋ መመስረት የሚያስችል የምርጫ መርሃ ግብር በመካሄድ ላይ ነው።

በመርሃ ግብሩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዘይነባ ሽኩር፣ የአዲስ አበባ ምርጫ ቦርድ ተወካዮች፣ተማሪዎች እና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

በምርጫ መርሃ ግብሩ የአፈ ጉባኤ፣ ምክትል አፈ ጉባኤና ጸሀፊ ምርጫ የሚካሄድ ሲሆን፣ የቋሚ ኮሚቴዎችንም የማደራጀት ስራ እንደሚከናወን ታውቋል።

የህጻናት ፓርላማ መደራጀቱ ህጻናት ዲሞክራሲያዊ ምርጫዎችን እንዲለማመዱ፣ የውሳኔ ሰጪነት ሚናን እንዲያዳብሩ እንዲሁም ለመብቱ የሚሟገት ትውልድን እውን በማድረግ ረገድ የላቀ ሚና እንዳለውም ተመላክቷል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዘይነባ ሽኩር እንዳሉት፣ የህጻናት ፓርላማ መደራጀቱ ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች ያሉት ወሳኝ እርምጃ ነው።

ፓርላማው የህጻናት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኝ ድምጽ መሆን የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰው፣የህጻናት መብቶች በተሻለ መልኩ እንዲተገበሩ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዳለው አብራርተዋል።

የህጻናት ፓርላማ እንዲጠናከር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።

ዛሬ የምትመረጡ ተመራጮች በስልጠና አቅማችሁ እንዲገነባ ከማድረግ ጀምሮ ያለንን ልምድ በማካፈል ውጤታማ እንድትሆኑ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነን ሲሉም ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የህጻናት ዘርፍ ኃላፊ እመቤት ተስፋዬ በበኩላቸው፣ በከተማ ደረጃ ፓርላማውን ለማቋቋም በትምህርት ቤቶች፣ ወረዳዎች እና ክፍለ ከተማዎች አስፈላጊውን ሂደት ማለፉን አስረድተዋል።

በዚህም በትምህርት ቤቶች፣ በወረዳዎች እና ክፍለ ከተማዎች መዋቅር የማደራጀት ስራ መከናወኑን መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

All reactions:

85Gashaw Abate, Muluken Getnet and 83 others

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review