የኦሮሚያ ፖሊስ ያሰለጠናቸውን የፖሊስ ኦፊሰሮችን አስመረቀ

You are currently viewing የኦሮሚያ ፖሊስ ያሰለጠናቸውን የፖሊስ ኦፊሰሮችን አስመረቀ

AMN- መጋቢት 14/2017 ዓ.ም

የኦሮሚያ ፖሊስ በሰንቀሌ የፖሊስ ሙያ ማሰልጠኛ እንስቲትዩት አሰልጥኖ ወደ ረዳት ኢንስፔክተርነት የተሸጋገሩ የፖሊስ ኦፊሰሮች፣ የትራፊክ ደህንነት ተቆጣጣሪዎች እና ማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት ኦፊሰሮችን አስመርቋል፡፡

የኦሮሚያ ፖሊስ የሰው ሃብት አስተዳደር እና ሎጅስቲክስ ዋና መምሪያ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል አበበ ለገሠ፣ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡

የኦሮሚያ ፖሊስ ራዕይ፣ ተልዕኮና ዓላማውን መሠረት በማድረግ በሀገርና በሕዝብ ላይ የሚሰነዘር ማንኛውንም ጥቃት በብቃት በመከላከል፣ ሰላም እና ደኅንነትን የማረጋገጥ ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡

በሕብረተሰቡ ላይ የትራፊክ አደጋ እንዳይደርስ አስቀድሞ በመቆጣጠርም በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢሮሚያ ፖሊስ አመራር እና አባላት ከሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከኢትየጵያ ፌደራል ፖሊስ እና ከሌሎች የፀጥታ ተቋማት ጋር በመቀናጀት የሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል፣ አጥንታቸውን በመከስከስና ደማቸውን በማፍሰስ የሕግ የበላይነትን እያስከበሩ፣ ሰላምና ደኅንነት እያረጋገጡ ይገኛሉም ብለዋል።

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ ጥናትና ምርምር በማድረግ፣ የአሠራር ከፍተቶችን እና የአቅም ውስንነቶችን በመለየት በተለያዩ ጊዜያት የትምህርትና ስልጠና ካሪኩለም በመቅረፅ ክፍተቶችን ለመቅረፍ በትጋት እየሠራ እንደሚገኝም ገልፀዋል፡፡

ወደ ረዳት ኢንስፔክተርነት ያደጉ እና በከፍተኛ ሰርተፍኬት የተመረቁ፣ የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ኦፊሰሮች እና የትራፊክ ደህንነት ተቆጣጣሪዎች በቀጣይ ህብረተሰቡን በጥብቅ ዲሲፕሊን እና በከፍተኛ ኃላፊነት ማገልገል እንዳለባቸውም ማሳሰባቸውን ከፌዴራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review