የጃፓን መንግስት ለኢትዮጵያ ከ63 ሺህ ኩንታል በላይ ዩሪያ የአፈር ማዳበሪያ ድጋፍ አደረገ

You are currently viewing የጃፓን መንግስት ለኢትዮጵያ ከ63 ሺህ ኩንታል በላይ ዩሪያ የአፈር ማዳበሪያ ድጋፍ አደረገ

AMN – መጋቢት 18/ 2017

የጃፓን መንግስት በኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመንና የዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል። በዛሬው ዕለትም 63 ሺህ 389 ኩንታል ዩሪያ የአፈር ማዳበሪያ ድጋፍ አድርጓል።

በርክክብ ስነ-ስርዓቱ ላይ የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው፣ በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሺቢታ ሂሮኖሪ እንዲሁም የኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ክፍሌ ወ/ማሪያም ተገኝተዋል።

የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት በጃፓን መንግስት የተደረገው የዩሪያ የአፈር ማዳበሪያ ድጋፍ ለታለመለት አላማ እንዲውል ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከክልሎች ጋር በመቀናጀት ለርሶአደሩና ከፊል አርብቶ አደሩ ተደራሽ እንዲሆን የክትትልና ድጋፍ ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በዛሬው ዕለት የተደረገው ድጋፍ ለአርሶና ከፊል አርብቶአደሩ አሁን ካለው ወቅታዊ የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ በግማሽ ቀንሶ የሚቀርብላቸው ሲሆን ይህም ትልቅ እገዛ እንደሚኖረው አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሺቢታ ሂሮኖሪ በበኩላቸው የጃፓን መንግስት የኢትዮጵያን ልማት በንቃት በመደገፍ በተለያዩ እቅዶች በተለይም በግብርና፣ በመሠረተ ልማት፣ በኢንዱስትሪ፣ በትምህርት እና በጤና ዘርፍ የዜጎችን ህይወት ለማሻሻል የበኩሏን አስተዋፆ እያበረከተች ትገኛለች ብለዋል።

አምባሳደሩ አያይዘውም በዛሬው ዕለት ድጋፍ የተደረገው ዩሪያ የአፈር ማዳበሪያ ለሚያስፈልጋቸው አርሶአደሮች እንዲደርሱና ጥቅም ላይ እንዲውሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት የጃፓን መንግስት በኢትዮጵያ በልማት ምስኮች ላይ ለሚያደርገው ሁለንተናዊ ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። መሰል ድጋፎችም የሁለቱን ሃገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት የሚያጠናክር መሆኑን ማንሳታቸዉን ከግብርና ሚኒስቴር ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review