እያንዳንዱ ትውልድ የራሱ አርአያና ጀግኖች አለው፤ በስፖርት ዓለምም እንደዚሁ ነው፡፡ በተለይም ከስፖርት ሜዳዎች ውጪ በሚሰሩት ስራ ምክንያት በአርአያነት የሚጠቀሱ የስፖርት ዓለም ሰዎች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። ስፖርተኞች ዝናቸውን ተከትሎ የመጣውን ሀብት ሳይሰስቱ ‘እንካችሁ’ የሚሉና በጎ ተፅዕኗቸውም ለሌሎች የተረፈ ታዋቂ ስፖርተኞች በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በሌላም በኩል በዘር፣ በኃይማኖት ወይም ሌሎች ጉዳዮች ሳቢያ ይደርስባቸው የነበረን ተፅዕኖ ተቋቁመው ለስኬት የበቁም በምሳሌነት ይጠቀሳሉ። በዚህ ጽሑፍም የኢድ አል ፈጥር በዓልን አስታክከን ተፅዕኗቸው ከስፖርቱ የተሻገረ ሙስሊም ስፖርተኞችን በጥቂቱ እናወሳለን፡፡
የጠንካራ ሰራተኝነት ምሳሌው ንጎሎ ካንቴ
ትውልደ አፍሪካዊና ፈረንሳዊው ንጎሎ ካንቴ እ.ኤ.አ መጋቢት 29 ቀን 1991 ተወለደ፡፡ ለእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ክለብ እና ለፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን አሁን ላይ ደግሞ በሳኡዲ አረቢያ አማካኝ ሆኖ የሚጫወት ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋች ነው። ካንቴ በ1980 ከማሊ ወደ ፈረንሳይ ከተሰደዱት ወላጆቹ በፓሪስ ከተማ ነው የተወለደው።
“ንጎሎ ምንም እንኳን ከፍተኛ ዝናን ያተረፈ ስፖርተኛ ቢሆንም ቀለል ያለ ኑሮ ይኖራል” ይሉታል በቅርበት የሚያውቁት፡፡ አነስተኛ ዋጋ ባለው መኪና መጓዝ እና በፈገግታ መኖር፣ የእሱ መገለጫ ነው። ታላቅነቱን ተጠቅሞ ለትውልድ ሀገሩ የደረሰም ትልቅ ሰው ነው።
ንጎሎ ካንቴ በማሊ ያለው የተበላሸ የህክምና አሰጣጥ ስርዓት ያበሽቀው የነበረ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ በ2025 በባማኮ ከተማ 5 ሚሊዮን ዶላር በማውጣት የህፃናት ህክምና አገልግሎት የሚሰጥ ዘመናዊ ሆስፒታል አስገንብቷል። ይህ ሆስፒታል በሺዎች ለሚቆጠሩ ህፃናት ተስፋ ሆኗል፡፡
በማሊ ያሉ ወጣቶች የተሻለ ዕድል እንዲያገኙ ንጎሎ ትምህርት ቤቶችን ይደግፋል። በሀገሪቱ በርካታ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት፣ መምህራንን ለመደገፍ እና መጽሐፍትና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍም ያደርጋል። “በልጅነቱ በድህነት ያየውን ጨለማ በትምህርት ብርሃን ለመቀየር እየተጋ ነው” ይላል አፍሪካን ኒውስ ላይ ያገኘነው ዘገባ፡፡
ንጎሎ ካንቴ በማሊ ያሉትን ማህበረሰቦች ለማጠንከር የራሱን ገንዘብ፣ ጊዜ እና ዝና ይጠቀማል። ከሆስፒታሎች እና ትምህርት ቤቶች ባሻገር ለድሆች የምግብ ድጋፍ፣ ለገበሬዎች የግብርና መሣሪያ እርዳታ እና ለሴቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ላይ አተኩሮ ይሰራል። በየዓመቱ ማሊን ይጎበኛል፣ የወገኖቹን ችግር በቅርበት ሆኖ ይከታተላል፤ እንባቸውንም ያብሳል። የተሰበረውን ለመጠገን፣ የተራበውን ለመመገብ እና የተረሳውን ለማስታወስ እንደሚኖር በመረጃው ተመላክቷል፡፡
እንስቷ አርአያ ናዋል ኤል ሙውዋኬል
በኦሎምፒክ ጨዋታዎች የመጀመርያዋ የሴቶች 400 ሜትር መሰናክል ውድድር ያሸነፈችው ሞሮኮዊቷ ናዋል ኤል ሙውዋኬል የመጀመሪያዋ አፍሪካዊ ሴት በኦሎምፒክ ወርቅ ያሸነፈች ስፖርተኛ ናት።
ለሙስሊም እና አፍሪካውያን አትሌቶች ፈር ቀዳጅ የነበረችው ናዋል፣ ‘ሴቶች በአትሌቲክስ ስፖርት ውጤታማ መሆን አይችሉም’ የሚለውን የረጅም ጊዜ እምነት የሻረች ስለመሆኗም ይመሰከርላታል፡፡ “ሴቶች በዘራቸው፣ በኃይማኖታቸው ወይም በፆታቸው የሚደርስባቸውን ተፅዕኖ ተቋቁመው ከግባቸው ለመድረስ ምንም ዓይነት ነገር እንደማይገድባቸው እንዲያውቁ እፈልጋለሁ” ስትልም ትናገራለች፡፡
“በሚያሳዝን ሁኔታ እኛ ሙስሊም ሴቶች ችሎታ እንዳለን የማስረዳቱ ኃላፊነት በኛ ላይ የወደቀ ነው” የምትለው ስፖርተኛዋ ብዙ ፈተናዎችን ተቋቁማ በተለያዩ ውድድሮች 17 ወርቅ ሜዳልያዎችን ለሀገሯ በማምጣት በተግባር አርአያነቷን አሳይታለች፡፡
ስፖርተኛዋ አፍሪካን ቱዴይ ከተሰኘ መገናኛ ብዙሃን ጋር ባደረገችው ቃለ ምልልስም ሴት ሙስሊሞች ሂጃባቸውን ሳያወልቁ በፈለጉት የስፖርት አይነት ላይ ተሳትፈው ውጤታማ መሆን ይችላሉ የሚል ጠንካራ አቋም እንዳላት አስረድታለች፡፡ ሴቶች እና ወጣት ልጃገረዶች ሂጃብ ለብሰውም ቢሆን ፍላጎታቸውን ለማሳካት እንዲፋለሙ ትመክራለች፡፡
አሁን ላይ በሀገሯ ሞሮኮና በዓለም አቀፍ የስፖርት ተቋማት ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃ በመስራት ከውድድር ውጪም በጎ ተፅዕኖዋን ቀጥላበታለች። ሴቶች የስፖርት ተሳትፏቸውን እንዲያሰድጉ ታግዛለች፤ በተለያዩ ሀገራት በመዘዋወር ስለ ስፖርትና ትምህርት አስፈላጊነት እንዲሁም ስለእኩልነት ታስገነዝባለች፤ በዚህ ሳቢያም ተፅዕኖዋ ከስፖርቱ የተሻገረ ሆኗል፡፡
ካቢብ ኑርማጎሜዶቭ
ሩሲያዊው የድብልቅ ማርሻል አርት ተጫዋች ካቢብ ኑርማጎሜዶቭ በስፖርቱ ዓለም በአርአያነት ከሚጠቀሱ ሙስሊም ስፖርተኞች መካከል ይገኝበታል፡፡ በዓለም ላይ ተወዳጅ በሆነው በዩኢሲ ማርሻል አርት ውድድር ላይ ያሸነፈ የመጀመሪያው ሙስሊም ነው፡፡
በዓለም ላይ በድብልቅ ማርሻል አርት ታሪክ ካቢብ ኑርማጎሜዶቭ በመልካም ስብዕና እና በአርአያነት ከሚጠቀሱ በጣት ከሚቆጠሩ ስፖርተኞች መካከል አንዱ ነው፡፡ በእርግጥ ኑርማጎሜዶቭን በጣም ልዩ የሚያደርገውና እኛም በዚህ ጽሑፍ ልናወሳው የወደድነው ስፖርታዊ ብቃቱ ብቻ ሳይሆን ከስፖርቱ ውጪ ያለው አሰደናቂ ባህሪ ነው፡፡ በደጋፊዎቹ ላይ ባሳደረው ተፅዕኖ እና ቁርጠኝነት፣ የታታሪ እና የስኬታማ ምሳሌ መሆን ችሏል፡፡ ጢማሙ ኑርማጎሜዶቭ ባሕላዊ የዳግስታኒ ልብስ ለብሶ ፈጣሪውን እያመሰገነ፣ በኃይማኖታዊ መንፈስ ተሞልቶ ሥልጠናውን የሚያቀጣጥል እና ከፍተኛ ስኬት ያስመዘገበ ስፖርተኛ ስለመሆኑ የ ዘ ጋርዲያን ዘገባ ያትታል፡፡
ያያ ቱሬ
ከቤልጅየም እስከ ግሪክ፣ ከፈረንሳይ እስከ ስፔን፣ ከስፔን እስከ እንግሊዝ ተዘዋውሮ በተጫወተባቸው ሁሉም ክለቦች ጣፋጭና የማይረሱ ድሎችን አጣጥሟል፡፡ የቢቢሲ የአፍሪካ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ክብርን ተጎናፅፏል፡፡ ያያ ቱሬ ከማንቸስተር ሲቲ ጋር በነበረው ቆይታ 3 የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ፣ አንድ ኤፍ.ኤ.ካፕ እና 2 የሊግ ካፕ ዋንጫዎችን ማንሳት ችሏል፡፡ በእነዚህ አሰደናቂ የእግር ኳስ ህይወት ውስጥ ታዲያ ለያያ ቱሬ ከባድ የነበረው ፈተና በቀለሙና በኃይማኖቱ ምክንያት ይደርስበት የነበረው የዘረኝነት ጥቃት ነው፡፡
የ20 ዓመት አዳጊ በነበረበት ወቅት ገና በለጋ ዕድሜው ነበር ይህንን ፈተና መጋፈጥ የጀመረው። ይጫወትበት የነበረው የዩክሬኑ ሜትሉር ዶኔስክ ደጋፊዎች ሳይቀር ማንነቱን እያነሱ አጸያፊ ስድብ ይሰድቡት እንደነበር የሚገልጸው ቱሬ፣ ጨዋታ መጫወት አቅቶት እስከማቆም ሊደርስ እንደነበር ጭምር በአንድ ወቅት ለመገናኛ ብዙሃን በሰጠው ቃለ ምልልስ ገልጾ ነበር፡፡
ያዩ ተሬ በወቅቱ እንደገለጸው እ.ኤ.አ በ2003 ይጫወትበት የነበረው ክለብ ደጋፊዎች ጭምር ‘አንተ ጥቁር፣ የማትረባ፣ ወደመጣህበት ተመለስ’ እያሉ ይሰድቡት እንደነበር ገልጾም ያውቃል፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች የዘረኝነት ጥቃት የተፈጸመበት ሲሆን ከእነዚህም መካከል ማንቸስተር ሲቲ ውስጥ በሚጫወትበት ወቅት ክለቡ በሩሲያ ከሲ.ኤስ.ኬ.ኤ ሞስኮ ጋር በሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያ ወቅት አጋጥሞት የነበረው የዘረኝነት ጥቃት አንዱ ነው፡፡
በቅርቡ ለሜቄዶኒያ ድጋፍ እንደሚያደርግ እንደነበር የተነገረለት ፈረንሳዊው ካሪም ቤንዜማ፣ ግብጻዊው ሞሐመድ ሳላህ እና ጥቁር አሜሪካዊቷ ኢብቲሃጅ ሙሀመድ እንዲሁም ሴኔጋላዊው ሳይድ ማኔና መሰል እውቅ ሙስሊም ስፖርተኞች እውቅናቸውን ተጠቅመው የበጎ አድራጎት ስራ በመስራትና ኢፍትሐዊነትን በመታገል በአርአያት ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በሳህሉ ብርሃኑ