የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቋሚነት የውጭ ምንዛሪ ጨረታ ሊያካሂድ ነው

You are currently viewing የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቋሚነት የውጭ ምንዛሪ ጨረታ ሊያካሂድ ነው

AMN – መጋቢት 22/2017

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በየሁለት ሳምንት መደበኛ እና ተከታታይ የውጭ ምንዛሪ ሽያጭ ጨረታ ማካሄድ እንደሚጀምር አስታወቀ።

መደበኛ ጨረታው ነገ በ50 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ መጠን እንደሚጀመርም ጠቁሟል።

ጨረታዎቹ ለሚቀጥሉት በርካታ ወራት እንደሚካሄዱ እና ዓላማውም የማዕከላዊ ባንኩን የተረጋጋ የውጭ ምንዛሬ ስርዓት ግብን ማሳካት እንደሆነ ባንኩ ገልጿል።

የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ከተጀመረበት ከሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም ወዲህ የወጪ ንግድ በመስፋፋቱ፣ የውጭ ሐዋላ በመጨመሩና የካፒታል ፍሰት በማደጉ ምክንያት የኢትዮጵያ የውጭ ክፍያ ሚዛን በከፍተኛ ደረጃ የመሻሻል አዝማሚያ ማሳየቱን በመግለጫው አስታውቋል።

የማዕከላዊ ባንኩ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ክምችት በታሪኩ ከፍተኛው መሆኑንም አመልክቷል።

በተለይ ከቅርብ ወራት ወዲህ፣ በሀገሪቱ ውስጥ ብቸኛው የወርቅ ገዥ ለሆነው ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የቀረበው የወርቅ መጠን ከፍተኛ እንደሆነና የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ክምችት ከተገመተው በላይ እንዲጨምር ማድረጉን ጠቅሷል።

ከውጭ ምንዛሪ ግኝቱ አንጻር ባንኩ በቀጣይ ወራት በመደበኛነት በየሁለት ሳምንቱ የውጭ ምንዛሪ ሽያጭ ጨረታዎችን ለማካሄድ መወሰኑን ነው ባንኩ ያስታወቀው።

ይህ አካሄድ በማዕከላዊ ባንክ እየተከማቸ ካለው የውጭ ምንዛሪ የተወሰነውን መጠን ለግሉ ዘርፍ ለማቅረብና የባንኩን የገንዘብ ፖሊሲ ዓላማ ለማሳካት እንደሚረዳ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በየሁለት ሳምንት የሚያወጣው የውጭ ምንዛሪ ጨረታ የውጭ ምንዛሪ ገበያን ለማረጋጋትና ሪፎርሙ ከተጀመረ ወዲህ መሻሻል እያሳየ የመጣውን የውጭ ክፍያ ሚዛን በይበልጥ ለማጠናከር እንደሚረዳ ታምኖበታል፡፡

በዚሁ መሰረት ነገ የ50 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ጨረታ ይካሄዳል።

ፍላጎቱ ያላቸው ባንኮች በተሰጠው የጊዜ ሰሌዳና በተቀመጠው አኳኋን የጨረታ ሰነዶቻቸውን እንዲያስገቡም ጥሪ አቅርቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review