የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ መደበኛ ያልሆነ ንግድን ስርዓት ለማስያዝ በወጣው ደንብ ላይ ውይይት አካሄደ

You are currently viewing የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ መደበኛ ያልሆነ ንግድን ስርዓት ለማስያዝ በወጣው ደንብ ላይ ውይይት አካሄደ

AMN-መጋቢት 23/2017 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ከአስራ አንዱም ክፍለ ከተማ ከተወጣጡ የንግዱ ማህበረሰብ ጋር መደበኛ ያልሆነ ንግድን ስርዓት ለማስያዝ በወጣው ደንብ እና ማንዋል ላይ ውይይት አካሂዷል።

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ፣ መደበኛ ያልሆነ የንግድ ስርዓት ላይ የተሰማሩትን ወደ መደበኛ የንግድ ስርዓት ለማስገባት ደንብ ቁጥር 184/2017 መውጣቱን ገልፀዋል፡፡

በመሆኑም ቀጥታ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የንግዱ ማህበረሰብ አካላት ጋር መወያየት ያስፈለገበት ምክንያት ደንቡን አውቀው እንዲያስፈፅሙ ለማድረግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአራዳ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጌታሁን አበራ፣ የከተማ አስተዳደሩ በርካታ የልማት ስራዎችን እየሰራ በመሆኑ አሁን ካለው የኮሪደር ልማት ስራ ጋር ኢ-መደበኛ ንግድ አብሮ ስለማይሄድ የንግድ ስርዓቱን ለማዘመን ደንብ መውጣቱ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

የንግዱ ማህበረሰብም ይህን ደንብ በባለቤትነት ወስደው ከአስተዳደሩ ጋር በጋራ እንዲሰሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ መደበኛ ያልሆነ ንግድ ስርዓት ማስያዝ ዳይሬክተር አቶ መለስ ተገኔ፣ መደበኛ ያልሆነ የጎዳና ላይ ንግድን ስርዓት ለማስያዝ የወጣውን ደንብ ቁጥር 184/2017 እና ማንዋል ሰነድ አቅርበዋል፡፡

በዚህም የወጣውን ደንብ እና መመሪያ አክብሮ መስራት ከንግዱ ማህበረሰብ እንደሚጠበቅ መናገራቸውን ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review