ኢትዮጵያ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በዲፕሎማሲያዊ መስኮች በታሪኳ ያልተሞከረውን አዲስ መንገድ የጀመረችበት ቀን ነው – ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)

You are currently viewing ኢትዮጵያ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በዲፕሎማሲያዊ መስኮች በታሪኳ ያልተሞከረውን አዲስ መንገድ የጀመረችበት ቀን ነው – ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)

AMN – መጋቢት 24/2017 ዓ.ም

ዛሬ መጋቢት 24 ነው፤ ኢትዮጵያ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በዲፕሎማሲያዊ መስኮች በታሪኳ ያልተሞከረውን አዲስ መንገድ የጀመረችበት ቀን መሆኑን የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ሚኒስትሩ በማህበራዊ የትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት፣ ያልተሄደበትን መንገድ በመደመር ፍልስፍና ቅኝት፣ በመሃል የፖለቲካ እይታ እየተመራች ከባለፈው በጎ በጎውን በመዉሰድ፣ ለነገው ትውልድ ዛሬ ላይ አዲስ አሻራ በማኖር አዲስ የከፍታ ምዕራፍ የጀመረችበት ዕለት ነው ብለዋል።

ሚኒስትሩ አክለውም መጋቢት 24 በውስብስብ ብዝሃነትና በርካታ ማንነት ምክንያት እንደ አንዳንድ ሀገሮች ተበታተነች ሲሏት እሷ ብዝሀነትን እንደ ጌጥ ተጠቅማ፣ ህብረ ብሄራዊ አንድነቷን ይበልጥ ማጠናከር የጀመረችበት እለት እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

ባለፉት የለውጥ ዓመታት በአምራች ኢንዱስትሪው፣ በማዕድን፣ በቱሪዝምና በሆስፒታሊቲ ዘርፍ፣ በከተማና መሰረተ ልማት ዝርጋታ እንዲሁም በዲጂታል ኢኮኖሚ ዘርፎች ኢትዮጵያ የተቃጣባትን ሁሉንም ችግሮች መክታ ልዕልናዋን በማረጋገጥ የማይታመን ፈጣን ለውጥና እድገት አስመዝግባለች ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡

ዜጎች የሰላም አየር እንዲተነፍሱ የዘመነ፣ የሰለጠነና በሀሳብ የበላይነት የሚመራ የፖለቲካ ሥርዓት ለመዘርጋት የተደረገዉ ጥረት ተስፋ ሰጪ ዉጤት ማምጣት መጀመሩን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ እነዚህን ድሎች ቆጥረን ዘላቂነቱን መጠበቅና ማስፋት ይገበናል ሲሉም አሳስበዋል፡፡

የዜጎችን ህይወት በሁለንተናዊ መልኩ ለመለወጥ፣ የሀገራችን እና የህዝባችንን ህልምና ርዕይ ለማሳካት መልካም ድሎቻችንን እያስቀጠልን፣ ጉድለቶቻችንን ደግሞ እያረምን በላቀ ትጋትና ቁርጠኝነት ልንረባረብ ይገባል ብለዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review