ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ በጋራ እንስራ – ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር)

You are currently viewing ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ በጋራ እንስራ – ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር)

AMN – መጋቢት 24/2017

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለውን ምክክር የሚያስገነዝብ መድረክ በባህር ዳር ከተማ አካሂዷል።

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር) ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ለዘላቂ ሰላም ግንባታ አሳታፊና አካታች ምክክር አስፈላጊ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል።

ኮሚሽኑ በአማራ ክልል የሚያካሂደው የአጀንዳ ልየታ መድረክ ውጤታማና ስኬታማ እንዲሆን ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ኮሚሽኑ እየሰራ ያለው ሥራ ውጤታማ እንዲሆን በጋራ እንስራ ሲሉም ዋና ኮሚሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) “በኢትዮጵያ የሰላም ግንባታ ሂደት የልሂቃን ሚና” በሚል ርዕስ የመወያያ ፅሁፍ ያቀረቡ ሲሆን፣ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ የልሂቃን ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኮሚሽነሩ የአማራ ክልል ልሂቃን ለሀገር እና ለክልላቸው ሰላም መረጋገጥ የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ ነው ያሳሰቡት።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፣ በአማራ ክልል የሚካሄደው የአጀንዳ ልየታ የተሳካ እንዲሆን የፖለቲካ እስረኞች የሚፈቱበት እንዲሁም የታጠቁ ኃይሎችና መንግሥት የተኩስ አቁም ስምምነት የሚያደርጉበት ሁኔታ እንዲፈጠር ኮሚሽኑ አቅሙን አሟጦ እንዲጠቀም ጠይቀዋል።

ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ(ፕሮፌሰር)፣ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገ/ስላሴ፣ ኮሚሽነር መላኩ ወ/ማርያምና ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) በጋራ ከመድረኩ ተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያዎችን መሰጠታቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review