በለውጡ ዓመታት በአዲስ አበባ የተከናወኑ የልማት ስራዎች የከተማዋን የብልጽግና ተምሣሌትነት በተግባር ያረጋገጡ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ ገለጹ፡፡
ሀገራዊ ለውጥ እውን የሆነበት 7ኛ ዓመት “ትናንት፣ ዛሬ እና ነገ ለኢትዮጵያ ልዕልና” በሚል መሪ ሀሳብ በዓድዋ ድል መታሰቢያ የፓናል ውይይት ተካሂዷል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ በዚሁ ወቅት፤ ባለፉት ሰባት የለውጥ ዓመታት በመዲናዋ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ አያሌ ስኬቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
ለሀገረ መንግስት ግንባታ መሠረት የጣሉ እና የኢትዮጵያን ቀጣይ መዳረሻ ብሩህ ያደረጉ አስደናቂ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል፡፡
በዚህም በፖለቲካ፣ኢኮኖሚ፣በማህበራዊ፣በዲፕሎማሲ፣በቴክኖሎጂ እንዲሁም በሰው ተኮር ስራዎች የሀገርን ትልም የሚያሳኩ ለውጦችና ድሎች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት ሰባት የለውጥ ዓመታት የተከናወኑ የልማት ስራዎችም የከተማዋን የብልጽግና ተምሣሌትነት በተግባር ያረጋገጡ ናቸው ብለዋል።
የመዲናዋን ነዋሪዎች ተጠቃሚነት በተግባር ያረጋገጡና የከተማዋን ገጽታ የቀየሩ መሆናቸውንም አክለዋል፡፡
በብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ሞገስ ባልቻ፤ ሀገራዊ ለውጡ የብሔራዊነት ትርክት እንዲጎላ ያደረገ እና የመደመር እሳቤን ለሀገር ያበረከተ ነው ብለዋል።
ለውጡ በፈተናዎች ውስጥ ዕድሎችን ፈልቅቆ በማውጣት ለብልጽግና ጉዞ ምቹ መደላድል መፍጠሩንም ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባም ለነዋሪዎች ምቹና ውብ የመኖሪያ፣ የሥራና የመዝናኛ ማዕከላትን ያካተቱ ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች እውን ሆነዋል ነው ያሉት፡፡
በውይይቱ በማህበራዊ ልማት ዘርፍ የተከናወኑ ስራዎችን አስመልክቶ ጽሑፍ ያቀረቡት አለማየሁ አረዳ (ዶ/ር) ባለፉት ሰባት ዓመታት በትምህርትና በጤና መሰረተ ልማት ተደራሽነትና አገልግሎት መስፋፋት ጉልህ ለውጥ መመዝገቡን ጠቅሰዋል።
በሴቶችና ወጣቶች ተጠቃሚነት፣በከተማ ደረጃ በቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራም እና በሌሎችም መስኮች የሕዝብን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል፡፡
በሰው ተኮር ተግባራት በዚህ ዓመት በመዲናዋ ብቻ ከ850 ሺህ በላይ ተማሪዎች የምገባ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰው፥ ከ1 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ደግሞ የትምህርት ቅሳቁስ ተደርጎላቸዋል ነው ያሉት።
ሌላኛው ፅሑፍ አቅራቢ አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ በበኩላቸው[ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣በገቢ አሰባሰብ፣በአምራች ዘርፍ፣ በቤቶች ግንባታ፣ በቱሪዝምና በሌሎችም ዘርፎች ትልቅ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል፡፡
በኮሪደር ልማት የተከናወኑ ስራዎች የከተማዋን ገጽታ የቀየሩ፣ የቱሪዝም ፍሰትን የጨመሩ እና የህዝቡን አኗኗር ያዘመኑ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ባቀረቡት የመወያያ ጽሑፍ፥ በለውጡ ዓመታት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ያስከበሩና ዓለም አቀፍ የተፅዕኖ አድማሷን ያሰፉ የዲፕሎማሲ ስኬቶች መኖራቸውን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ቀጣናውን በኤሌክትሪክ ሃይልና ሌሎች መሰረተ ልማቶች የማስተሳሰር ስራን አጠናክራ መቀጠሏንም ገልጸዋል።
ለአፍሪካ ኢኮኖሚያዊ ውህደት ጉልህ ሚና ያለው አህጉራዊ የነጻ ንግድ ቀጣና እውን እንዲሆንም ኢትዮጵያ በግንባር ቀደምትነት ወደ ትግበራ እየገባች ነው ብለዋል።
በውይይቱ የከተማዋ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች፣ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮችን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መገኘታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡