የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ከሰሞኑ ወደ አሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ የ10 በመቶ ታሪፍ አስተላልፈዋል፡፡
ውሳኔው በዓለም የንግድ ሥርዓት ላይ ጫና እንደሚያሳድር የዘርፉ ባለሙያዎች እየገለፁ ይገኛል፡፡
ትራምፕ የጣሉትን አዲሱን ታሪፍ በርካቶች የተቃወሙት ሲሆን፣ አውሮፓ ውሳኔው ከወዲሁ ከባድ የኢኮኖሚ ማዕበል የሚያስከትል መሆኑን አስታዉቃለች፡፡
ጣሊያን እርምጃው የተሳሳተ ነው ስትል፣ አውስትራሊያ ደግሞ ዉሳኔዉ ከአንድ ወዳጅ የማይጠበቅ ድርጊት ነዉ ብላዋለች፡፡
እጅግ ከፍተኛ ታሪፍ የተጣለባት ቻይና በበኩሏ፣ የታሪፍ ማሻሻያውን ከበቀል እርምጃ ቆጥራዋለች፡፡
ፕሬዝዳንት ትራምፕ አሜሪካ ባለፉት 10 ዓመታት ሚዛናዊ ባልሆነ የዓለም ንግድ ሥርዓት ምክንያት በወዳጅ፣ በቅርብና በሩቅም ባሉ ሀገራት ጭምር ስትበዘበዝ መቆየቷን ትላንት ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ሠራተኞች፣ ለካቢኔ አባላቱ እና ለጋዜጠኞች ባደረጉት ንግግራቸው ላይ አስታውቀዋል፡፡
“ዛሬ በአሜሪካ ላይ የሚደርሰው ተደጋጋሚ ጉዳት የሚያበቃበት ታሪካዊ ቀን ነው” ሲሉም ገልጸዋል፡፡
እለቱም የአሜሪካ ኢንዱስትሪ ዳግም የተወለደበት እና የአሜሪካ መፃዒ ዘመን የተበየነበት ተደርጎ በታሪክ እንደሚታወስ ገልጸዋል፡፡
በሁሉም የዓለም ሀገራት ላይ ወደ አሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ የ10 በመቶ ታሪፍ ትግበራ ከቀናት በኋላ ማለትም ሚያዝያ 5 ቀን 2025 ላይ ይጀመራል፡፡
10 በመቶ ቀረጥ ከተጣለባቸው የዓለም ሀገራት በተጨማሪ በልዩ ሁኔታ ከፍተኛ ታሪፍ የተጣለባቸው ሀገራትም ይፋ ተደርገዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት 20 በመቶ፣ ቻይና 34 በመቶ ፣ ቬትናም 46 በመቶ እንዲሁም ታይላንድ 36 በመቶ ቀረጥ የተጣለባቸው ሀገራት ናቸው፡፡
በልዩ ሁኔታ ቀረጥ የተጣለባቸው ሀገራት ላይ ከአራት ቀናት በኋላ እርምጃው ይተገበራል፡፡
ምንጭ፡- ቢቢሲና አልጀዚራ