የጫኝ እና አዉራጅ ህግና ደንብ ወጥቶ ወደ ስራ ከተገባ ብኋላ፣ ከዚህ ቀደም ህዝቡ ሲያነሳቸው የነበሩ ቅሬታዎች መቀነሳቸውን የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳዳር ቢሮ አስታወቀ፡፡
ቢሮዉ በአራዳ፣ በጉለሌ፣ በልደታ እና በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ለሚገኙ ጫኝ እና አዉራጆች ስልጠና እየሰጠ ይገኛል፡፡
የመዲናዋ ነዋሪዎች ንብረታችውን በሚያንቀሳቅሱበት ወቅት አላስፈላጊ ዋጋ በጫኝ እና አውራጆች ሲጠየቁ፣ ለእንግልት እና ምሬት ሲዳረጉ እንደነበርም ተመላክቷል፡፡
ይህን ችግር ለመቅረፍም የአዲስ አበባ ከተማ ሰላም እና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ አገልግሎቱ በሕግ እና ሥርዓት እንዲመራ ህግና ደንብ አውጥቶ ወደ ስራ መግባቱ ይታወሳል፡:
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ ሚደቅሳ ከበደ፣ ሕግ እና ደንቡ ከወጣ በኋላ በህብረተሰቡ ዘንድ ይደርስ የነበረዉ እንግልት ቀንሷል ብለዋል::
ሕግና እና ደንብን አክብረዉ የሚሰሩ በአርአያነት የሚጠቀሱ ጫኝና አዉራጆች መፈጠራቸዉንም አቶ ሚደቅሳ ከበደ ተናግረዋል::
የስነ ምግባር ጉድለት ያለባቸዉ እና አሁንም ከሕግ እና መመሪያ ውጭ የሚሰሩ ጫኝ እና አዉራጆች መኖራቸዉን ሃላፊው ጠቁመው፣ በእነዚህ ማህበራት ላይ የተለያዩ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም ህግ የማስከበር ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
በቴዎድሮስ ይሳ