ኢትዮጵያና ፓኪስታን በአቪዬሽን ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ለማሳደግ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግሥቴ እና በኢትዮጵያ የፓኪስታን አምባሳደር አቲፍ ሻኒፍ ምክክር አድርገዋል።
በውይይቱ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግሥቴ፣ ፓኪስታን ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመሥራት ያሳየችው ፍላጎት የሚደገፍ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በጊዜያዊ ፈቃድ ወደ ፓኪስታን እያደረገ ያለውን በረራ አስፈላጊ ጉዳዮች ተሟልተው በቋሚነት ወደ ተለያዩ መዳረሻዎች ለመብረር እንዲችል የአየር አገልግሎት ስምምነት መፈራረም እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ ከአየር ትራንስፖርት አገልግሎት በተጨማሪም በሌሎችም የአቪዬሽን ዘርፎች በጋራ መሥራት ከአቪዬሽን ባሻገር ለሁለቱም ሀገራት ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ተጨማሪ አቅም እንደሚሆንም አብራርተዋል።
የፓኪስታን አምባሳደር በበኩላቸው ፓኪስታን ከኢትዮጵያ ጋር ዘረፈ ብዙ ትብብሮችን ማድረግ እንደምትፈልግ ጠቁመው፣ በአቪዬሽን ዘርፍ ከአየር ትራንስፖርት አገልግሎት በተጨማሪ በሜዲካል ቱሪዝም፣ በሰው ኃይል ሥልጠና እና በአቪዬሽን ቴክኖሎጂ በጋራ ለመሥራት ፍላጎት እንዳላት አንስተዋል።
ፓኪስታን እንደ ህንድ፣ ታይላንድ እና ማሌዢያ የሜዲካል ቱሪዝም ሰፊ አቅም እንዳላት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድም ከካራቺና ኢስላምአባድ በተጨማሪ ወደ ላሆር እንዲበርና በሃጂና ኡምራ ጉዞ ወቅትም የበረራ አገልግሎት እንዲሰጥ ፍላጎት መኖሩን አምባሳደሩ ጠቁመዋል።
በሂደት ላይ ያለው የአየር አገልግሎት ስምምነትን ተደራድሮ የመፈራረም የመረጃ ግንኙነት በማጠናቀቅ በቅርቡ ለመፈጸም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
ከ100 የማያንሱ የፓኪስታን ባለሀብቶች በፈረንጆቹ ከግንቦት 15 እስከ 17 ቀን 2025 በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ የወጪ ንግድ ኤግዝቪሽን እና ባዛር እንደሚያካሂዱ መግለጻቸውን ከሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።