የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ለተለያዩ ተግባራት የሚውል ከ18 ሄክታር በላይ መሬት በሊዝ ጨረታ ለማስተላለፍ የሰነድ ማስረከቢያ መርሐ-ግብር እያካሄደ ይገኛል።
የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማት አስተዳደር ቢሮ የለማ መሬት ማስተላለፍ የሊዝ ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ጫሊ አብርሃም፣ ቀደም ባሉት ዓመታት በአሰራር ስርአቱ ክፍተት የመሬት ጨረታ ሳይወጣ መቆየቱን አንስተዋል፡፡
በቅርቡ በተደረገው ሪፎርም የአሰራር ስርአቱን በማዘመን እና የለሙ መሬቶችን በማጥናት ለተለያዩ ግልጋሎቶች የሚውሉ መሬቶችን ለጨረታ ክፍት በማድረግ ለተከታታይ አራት ዙር ማስተላለፍቸውን ተናግረዋል።
በ5ኛው ዙር ለጨረታ የቀረቡ መሬቶች በመዲናዋ በዘጠኝ ክፍለ ከተሞች የሚገኙ መሆናቸውን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፣ ይህም አመኔታ ያለው እና ግልፅ እንዲሆን ተጫራቾች ሁሉንም ሂደታቸውን በኦንላይን እንዲያደርጉ ማስቻሉን ተናግረዋል።
የጨረታ ሂደቱ ከብልሹ አሰራሮች የፀዳ እንዲሆን ከእጅ ንክኪ የራቀ መሆኑን ያነሱት ዳይሬክተሩ በዚህም ተጫራቾችና ወኪሎቻቸው በኦላይን ሁነቱን በግልፅ እንዲከታተሉ እንዳስቻላቸውም ተናግረዋል።
5ኛው ዙር የመሬት ሊዝ የጨረታ ሰነድ መመለሻ ጊዜም ዛሬ እስከ ቀኑ 11:30 ድረስ እንደሚቆይ ቢሮው አስታውቋል።
በራሄል አበበ