የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የአየር ብክለትን ከመቀነስ ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዳላቸው መረጃዎች ያመላክታሉ
በዓለማችን በዓመት በአየር ብክለት ሳቢያ 8 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሰዎች ለህልፈት እንደሚዳረጉ መረጃዎች ያመላክታሉ። የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) የከባቢያዊ አየር ለውጥ መንስኤዎች እና መፍትሔዎቹ በሚል ርዕስ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2024 ባወጣው ጥናት ጉዳዩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ጠቅሶ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙዎችን ለሞት እና ለከፋ የጤና እክል እየዳረገ መሆኑን አትቷል።
ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት ዋነኞቹ የጥቃቱ ሰለባዎች መሆናቸውን የሚያትተው ጥናቱ፣ ከደካማ የአመጋገብ ስርዓት በመቀጠል ሁለተኛው የህፃናት ገዳይ ምክንያት እንደሆነም አስፍሯል፡፡
በተመሳሳይ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2024 ይፋ የሆነው የስቴት ኦፍ ግሎባል ኤይር (State of Global Air) ሪፖርት፣ በአየር ብክለት ምክንያት ለሞት ከሚዳረጉት ሰዎች ውጭ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩት ለተለያዩ መርዛማ ንጥረ ነገሮች ተጋልጠው ቋሚ ህመምተኞች እንደሆኑ አመላክቷል። ይህም በጤና ስርዓት፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ጫና እንዳስከተለ አስፍሯል። በዚህ ሪፖርት መሠረት፣ ችግሩ የፅንስ መቋረጥን ጨምሮ በጨቅላ ህፃናት ጤና ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት አስከፊ ሆኗል። በ2021 ለህልፈተ ህይወት ከተዳረጉ ሰዎች መካከል 700 ሺህ ያህሎቹ ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት ናቸው፡፡
ሪፖርቱ በ200 የዓለም ሀገራት ያለውን የአየር ብክለት ሁኔታ በማጥናት የተጠናቀረ ሲሆን፣ በእነዚህ ሀገራት ውስጥ ከታየው ግኝት አንፃር ዓለም በአስከፊ የአየር ብክለት ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች፡፡ ብዙዎች የልብ፣ የስትሮክ፣ የስኳር፣ የሳምባ ነቀርሳ እና የሌሎች ህመሞች ሰለባ ሆነዋል፡፡
ታድያ የአየር ብክለትን የሚያስከትሉ በርካታ ምክንያቶች እንዳሉ የሚያትተው ሪፖርቱ፣ አንዱ ነዳጅ ከሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች የሚመነጨው በካይ ጋዝ እንደሆነ አስፍሯል፡፡ ታዳሽ የኃይል አማራጮችን መጠቀም ደግሞ ችግሩን ለማቃለል ከተጠቆሙ መፍትሔዎች አንዱ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ለዚህ ችግር መቃለል የሚጠበቅባትን አስተዋፅኦ ለማበርከት ጅምር እንቅስቃሴ ላይ ትገኛለች፡፡ በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ዘርፍ የ10 ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ 4 ሺህ 800 የኤሌክትሪክ አውቶቡሶች እና 148 ሺህ የኤሌክትሪክ አውቶሞቢሎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ተወጥኖ እየተሰራ መሆኑን በማሳያነት ማንሳት ይቻላል። በዚሁ ጊዜ ውስጥ በአዲስ አበባ ከተማ 1 ሺህ 176 እንዲሁም በክልል ከተሞች ደግሞ 1 ሺህ 50 በድምሩ 2 ሺህ 226 የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቻርጅ እስቴሽን ለመስራት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑም ልብ ይሏል፡፡
ለመሆኑ በአዲስ አበባ ከተማ የአየር ብክለት ሁኔታ ምን ይመስላል? የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ወደ አገልግሎት የማስገባት ተግባርስ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል? የሚሉ ነጥቦችን መፈተሽ የዚህ ፅሑፍ ዓላማ ነው፡፡
በአረጁ ተሽከርካሪዎች ሳቢያ አዲስ አበባ ቀላል ለማይባል የአየር ብክለት እንደምትጋለጥ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡ በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በአየር ንብረት ለውጥ የአማቂ ጋዝ ቅነሳና አረንጓዴ ቴክኖሎጂ ማስፋፊያ ቡድን መሪ አቶ ሰለሞን መለሰ በነዳጅ ከሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ የካርቦን ልቀት በመጨመሩ የአየር ብክለት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ጠቁመዋል፡፡ ከ20 ዓመት በላይ የተነዱ ተሽከርካሪዎች በከተማዋ በመኖራቸው ችግሩን እያባባሱት ይገኛሉ፡፡ ይህም በነዋሪዎች ላይ የተለያዩ የጤና እክሎች እንዲፈጠሩ ስለማስቻሉ ተመላክቷል፡፡
በአራዳ ክፍለ ከተማ የወረዳ 3 ነዋሪ የሆኑት አቶ ለገሰ ወዳጅነው በአየር መቀያየር ሳቢያ ደጋግሞ ለሚያስቸግራቸው የአስም ህመም ህክምና ፍለጋ ወደ የካቲት 12 ሆስፒታል በመጡበት ወቅት ነው ያገኘናቸው። ቅስፍ አድርጎ ከሚያስጨንቃቸው ሳል ጋር እየታገሉ የህመማቸው ምክንያት ከተሽከርካሪዎች ከሚመነጭ በካይ ጋዝ ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል በመጠቆም፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በስፋት ጥቅም ላይ ለማዋል የተያዘውን ውጥን ስኬታማነት በጉጉት እንደሚጠብቁም ተናግረዋል፡፡
አቶ ሰለሞን በማብራሪያቸው፣ የከተማዋ የአየር የብክለት መጠን የዓለም ጤና ድርጅት ካስቀመጠው እና ኢትዮጵያ ካስቀመጠችው የደረጃ ልኬት በላይ የሚሆንባቸው አጋጣሚዎች አሉ ብለው፣ በዚህም ሳቢያ እንደ አስም፣ ጉንፋን እና ሌሎች የመተንፈሻ አካላት በሽታዎች እየጨመሩ መሆኑን አመላካች ውጤቶች መኖራቸውን ገልፀዋል፡፡
ከችግሩ አሳሳቢነት አንፃር የተለያዩ የመፍትሔ አማራጮችን መከተል ይገባል፡፡ አንዱ አመራጭ የካርቦን ልቀትን መቀነስ ሲሆን፣ በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን መቀነስና በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ቁጥር ማበራከት ያስፈልጋል፡፡ ይህም በዕቅድ ተይዞ እየተሰራበት ስለመሆኑ ከባለስልጣኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
መንግስት በቀጣይ ጊዜያት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ወደ 30 በመቶ የማድረስ እቅድ ያለው መሆኑን ከባለስልጣኑ ያገኘነው መረጃ ያትታል። ባሰለፍነው ሳምንት ወደ አገልግሎት የገቡት 100 የኤሌክትሪክ አውቶብሶችም የዚሁ ውጥን አካል መሆናቸው ተነግሯል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ ያለውን የብዙሃን ትራንስፖርት እጥረት እና የነዋሪዎችን እንግልት የሚቀንሱ 100 ዘመናዊ የኤሌክትሪክ አውቶቡሶችን በመግዛት ወደ ስምሪት ማስገባቱ ይታወሳል፡፡

በዚሁ ዕለት የከተማዋ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት፣ “እነዚህ አውቶቢሶች ከአየር ብክለት ነፃ፣ ምቹ፣ በአንድ ጊዜ በርካታ ሠው ማጓጓዝ የሚችሉ፣ ዘመናዊና ተደራሽ፣ ወጪ ቆጣቢ፣ አስተማማኝ፣ ፈጣን አገልግሎት የሚሰጡ እንዲሁም ለነዳጅ ይወጣ የነበረውን ወጪ የሚቀንሱ ናቸው” ማለታቸው ይታወሳል። ከ6 ወር በፊትም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በስሩ ለሚገኙ መስሪያ ቤቶችና ወረዳዎች የሚያገለግሉ 150 የኤሌክትሪክ ሚኒ ባስ ተሽከርካሪዎችን ገዝቶ መስጠቱ አይዘነጋም፡፡ እነዚህ ሚኒ ባስ ተሽከርካሪዎች የከተማዋ የትራንስፖርት አገልግሎት ከአየር ብክለት የፀዳ እንዲሆን ለሚሰራው ስራ ትልቅ እገዛ አላቸው፡፡
በርክክቡ ወቅት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባስተላለፉት መልዕክት ተሽከርካሪዎቹ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ አንድ አካል ሲሆኑ ወጪን በመቀነስ ረገድም ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም የከተማ አስተዳደሩ ከተማዋን ዘመናዊ፣ ለነዋሪዎቹ ምቹና ማህበረሰቡ የሚጠብቀውን ተገቢ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የሚሠሩ ስራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ ያለውን የትራንስፖርት ችግር የሚያቃልሉ 100 ዘመናዊ የኤሌክትሪክ አውቶቡሶችን በመንግስት እና በግል አጋርነት ወደ አገልግሎት ማስገባቱ የትራንስፖርት አገልግሎትን በማቀላጠፍ ረገድ አርዓያነት ያለው ተግባር መሆኑን ተናግረዋል
ከትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ እንደሚያመላክተው፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ቁጥር ለማበራከት የተለያዩ ማበረታቻዎች ተዘጋጅተው እየተተገበሩ ይገኛሉ። ለአብነት ያህል ሙሉ በሙሉ ተገጣጥመው ወደ ሀገር ውስጥ ለሚገቡ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የሚከፈለው ታክስ 15 በመቶ፣ በከፊል ተገጣጥመው ለሚገቡ ደግሞ 5 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ የሚገጣጠሙ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ደግሞ ከታክስ ነጻ
ተደርገዋል።
ይህም በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ላይ ከሚጣላው ታክስ ጋር ሲነጻጸር እጅግ አነስተኛ በመሆኑ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ለማበረታታት እየተሰራ ያለውን ስራ ማሳያ ነው፡፡ የጥገና ማዕከል እና የቻርጅ ስቴሽን እጥረት እንዳይኖርም እየተሠራ መሆኑን መረጃው ያትታል፡፡
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የአየር ብክለትን ከመቀነስ ባለፈ ቀላል የማይባል ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዳላቸው ኢ.ቪ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ጥገና አገልግሎት መስጫ ማዕከል ስራ አስኪያጅ ኢንጂኒየር ዳዊት አካሉ ይናገራሉ፡፡ ኢንጂኒየሩ በሰጡን ሙያዊ ማብራሪያ፣ ትልቁ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ጥቅም ለነዳጅ የሚውለውን የውጭ ምንዛሬ ያስቀራሉ፡፡ የጥገና ሂደታቸውም ቀልጣፋና ጊዜ ቆጣቢ ነው፡፡ ይህም ባለንብረቶችን ከተጋነነ የጊዜ ብክነትና ወጪ ይታደጋል፡፡
በተለይ ከፍተኛ የታዳሽ እምቅ ኃይል ላላት ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አዋጭነት ከጥያቄ ውስጥ የሚገባ አለመሆኑን የጠቆሙት ኢንጂኒየሩ፣ በተለይ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እና ሌሎች የኃይል ማመንጫ አማራጮች እየተባረከቱ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በስፋት ወደ አገልግሎት ማስገባት ብልህነት ነው ይላሉ፡፡ ይህም የዓለምን ገበያ የተቆጣጠሩት የተሽከርካሪ አምራች ድርጅቶች ፊታቸውን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ወደ ማምረት እያዞሩ ከመሆኑ ጋር ተደማምሮ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸውን የጎላ ያደርገዋል ብለዋል።
በተካልኝ አማረ