ለጤናማ የአኗኗር ዘይቤ በር የከፈተው ልማት

You are currently viewing ለጤናማ የአኗኗር ዘይቤ በር የከፈተው ልማት

በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ ልማቶች ጤናማ ማህበረሰብ በመፍጠር ረገድ ያላቸው አበርክቶ ትልቅ እንደሆነ ተገልጿል

አቶ ሰለሞን ነገሰ አራት ኪሎ አካባቢ፣ መንገድ ዳር ለማረፊያነት ከተዘጋጁ ወንበሮች አንደኛው ላይ ቁጭ ብለው ከጓደኛቸው ጋር ያወጋሉ፡፡ በእግራቸው ላይ ጉዳት ስለደረሰባቸውና ረጅም ርቀት በእግር ለመንቀሳቀስ ስለሚቸገሩ ብዙውን ጊዜ ብስክሌት አዘወትረው ይጠቀማሉ፡፡

አምስት ኪሎ አካባቢ ለበርካታ ዓመታት መኖራቸውን እና  አካባቢው ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ የሚታይበት፣ የእግረኛ መንገድ የሌለበት፣ አይደለም ለመኖር ለማየት እንኳን የሚቀፍ ወንዝ ያለበት እንደነበር በማስታወስ፣ ዛሬ ላይ በኮሪደር ልማቱ ለማመን በሚከብድ መልኩ ገፅታው መቀየሩን ይናገራሉ፡፡

“አካባቢው ቆሻሻ በመሆኑ እንኳን ልናርፍበት ስናልፍበት የምንፀየፈው ነበር። በተለይ የወንዝ ዳርቻዎች አካባቢ የጤና ስጋት ነበሩ፡፡ አሁን የምንተነፍሰው አየር ንፁህ ሆኗል፤ በየአካባቢው ዕፅዋት ተተክለዋል፡፡ ይህም ሙቀትን መቆጣጠር ያስችላል፡፡ አሁን አካባቢው በትክክልም  ውብ መልክና ገፅታን ተላብሷል” ሲሉ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል፡፡

አቶ ሰለሞን ብዙውን ጊዜ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ብስክሌት የሚጠቀሙ ናቸው። ሆኖም ከዚህ ቀደም የከተማዋ መንገዶች በብስክሌት ለመንቀሳቀስ ያልተመቹና ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ የሚስተዋልባቸው ስለነበሩ ለአደጋ ያጋልጣሉ፡፡ አሁን ላይ ለብስክሌት ራሱን የቻለ መንገድ በመሰራቱ እንቅስቃሴ በማድረግ አካላዊና አእምሯዊ ጤንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን እንዳስቻላቸው ተናግረዋል፡፡

ሌላኛው ከፒያሳ ወደ አራት ኪሎ በእግሩ ሲንቀሳቀስ ያገኘነው በጉለሌ ክፍለ ከተማ ጳውሎስ አካባቢ ነዋሪ የሆነው ወጣት ደምስ ሀይሉም ከዚህ ቀደም ያን ያህል በእግር የመንቀሳቀስ ልምድ እንዳልነበረው ይናገራል፡፡ በኮሪደር ልማቱ የተሽከርካሪ፣ የእግረኛና ሳይክል መንገዶች ለየብቻ ተለይተው ተሰርተዋል፣ አረንጓዴ ሳሮችና ዛፎች ተተክለው የሚታዩበት አካባቢ በመፈጠሩ በእግር ጉዞ ማድረግን ባህል እንዲያደርገው ማገዙን ገልፆልናል። አሁን ከፒያሳ ወደ አራት ኪሎ ወይም ከአራት ኪሎ ወደ ፒያሳ እንቅስቃሴ ሲያደርግ በአብዛኛው ታክሲ አይጠቀምም፡፡ መንገዶቹ በእግር ጉዞ በማድረግ ጤናን ለመጠበቅ፣ ከስራ በኋላ የደከመ አእምሮን ፈታ ለማድረግ ምቹ ሆነዋል ይላል፡፡

የከተማዋ ወንዞችም በጣም ከመበከላቸው የተነሳ ምንም ዓይነት አገልግሎት የማይሰጡበት ደረጃ ደርሰው ነበር፡፡ በወንዝ ዳርቻ ልማቱ አረንጓዴ እየለበሱ መምጣታቸው ሌላው ጥቅማቸውን ትተን ለእይታም ደስ የሚያሰኙ እንዳደረጋቸው ይገልጻል፡፡    

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ዋነኛ ማዕከል፣ የአፍሪካ መዲናና የዓለም የዲፕሎማሲ ከተማ የሆነችው አዲስ አበባ ስሟንና ደረጃዋን ወደምትመጥን ከተማ ለመሸጋገር በርካታ ልማቶች እየተከናወኑ ይገኛሉ። በዚህ ረገድ ከአንድ ዓመት በፊት የተጀመረው ከማዕከላዊ የከተማዋ አካባቢዎች በመነሳት በስፋት እየተሰራበት ያለው የኮሪደር ልማት ይጠቀሳል፡፡

በኮሪደር ልማት ከፍተኛ የህዝብ እንቅስቃሴና መጨናነቅ ያለባቸው ፒያሳ፣ አራት ኪሎ፣ ቀበና፣ ሜክሲኮ፣ ሳር ቤት፣ መገናኛ፣ ሲኤምሲ ያሉ ነባርና አዳዲስ የከተማዋ አካባቢዎች፣ ዛሬ ላይ የተለየ ውበትና ማራኪ ገፅታን ተላብሰዋል። የተሽከርካሪ መንገዶች ሰፍተው፣ አዳዲስና ሰፊ የእግረኛ መንገዶች፣ የሳይክል መንገዶች፤ ደረጃቸውን የጠበቁ የህዝብ መፀዳጃ ቤቶች ተገንብተዋል፡፡ በርካታ አረንጓዴ ቦታዎች ተፈጥረዋል፡፡

ፅዱ፣ ውብና ሰፊ የእግረኛ መንገዶች፣ በየመንገዶቹ ዳርቻ ያሉ አረንጓዴ ሳሮችና እፅዋቶች፣  ነዋሪዎች ንጹህ አየር እየሳቡ፣ ሲደክማቸው ወንበር ላይ አረፍ እያሉና እየተዝናኑ በእግራቸው  መንቀሳቀስ የሚችሉበትን ዕድል ሰጥተዋል፡፡ ለዚህ ከፒያሳ እስከ አራት ኪሎ ወይም ከአራት ኪሎ ወደ ፒያሳ በሚወስደው መንገድ በተለይ ጠዋትና በስራ መውጫ ሰዓት እንደ ደምስ ያሉ ነዋሪዎች በእግር እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ማየት በቂ ነው። በርካታ ወጣቶች፣ አረጋውያን፣ ሴቶች፣ ወንዶች በእግር ጉዞ ሲያደርጉ ይስተዋላል፡፡

የኮሪደር ልማት የከተማዋን መንገዶችና አካባቢን ብቻ አይደለም የቀየረው። በተፋፈገና የተጨናነቀ ሰፈር የጤናና ደህንነት ስጋት በሚፈጥር ሁኔታ ይኖሩ የነበሩ ሰዎችን አኗኗርም ቀይሯል። በአንድ ግቢ በርካታ ቤተሰብ እየኖረ፣ በጋራ አንድ መፀዳጃ ቤት የሚጠቀምበት፣ አንድ ጠባብ ክፍልን እንደ ማዕድ እና ሳሎን የሚገለገልበት፣ በቂ መናፈሻና መስኮቶች በሌለበት ሁኔታ የሚኖሩበት ሁኔታንም ለውጧል፡፡

በኮሪደር ልማቱ መንገዶች፣ ህንፃዎች ብቻ ሳይሆን ወንዞችና የወንዝ ዳርቻዎችም ጭምር ነው ቀን የወጣላቸው፡፡ በሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማትም በቀበና ወንዝ ዳርቻ (20 ኪሎ ሜትር) እንዲሁም ከእንጦጦ እስከ ፒኮክ (21 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር) የሚሸፍን ልማት እየተሰራ መገኘቱን በማሳያነት ማንሳት ይቻላል። ቆሻሻ፣ አፍንጫን የሚሰነፍጥ ሽታ፣ ወደ ጥቁርነት ተቀይረው የነበሩ ወንዞች ተፈጥሯዊ ወዛቸውን መያዝና መጥራት ጀምረዋል፡፡ 

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፣ የወንዝ ዳርቻ ልማቱን በተመለከተ ከሁለት ሳምንት በፊት በሰጡት አስተያየት፣ “የወንዞች ብክለት መሰረታዊ የጤና ችግር መሆኑን ስንሰማ ደንግጠናል፣ ከምንም በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ በመረዳት 42 ኪሎ ሜትር የወንዝ ዳርቻ እያለማን ነው ያለነው። እንደ ሌላው ኮሪደር በጣም ፈጥኖ የሚያልቅ ባይሆንም በተያዘው በጀት ዓመት ለመጨረስ በከፍተኛ ቁርጠኝነትና እልህ እየሰራን ይገኛል፡፡ ምክንያቱም የሰውን ሕይወት የመታደግ ጉዳይ ነው” ብለዋል፡፡

ሌላው ከተማዋ ትኩረት ሰጥታ እየሰራችበት ያለው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ነው፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ2011 ዓ.ም በተጀመረውና በየዓመቱ ተግባራዊ እየሆነ ባለው የአረንጓዴ አሻራ አዲስ አበባም ንቁ ተሳትፎ እያደረገችና የደን ሽፋኗም እየጨመረ ይገኛል፡፡

አዲስ አበባ ስትቆረቆር በአረንጓዴነቷ እና ባላት የደን ሽፋን የምትታወቅ ቢሆንም፣ በየጊዜው ያለ እውቀትና ግንዛቤ በተደረገው የደን ጭፍጨፋ የደን ሽፋኗ በ2010 ዓ.ም በነበረው መረጃ ወደ 2 ነጥብ 8 በመቶ ወርዶ ነበር፡፡ የአዲስ አበባ የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገጽ ላይ የወጣው መረጃ እንደሚያሳየው፣ ባለፉት ስድስት ዓመታት በተሰራው የአረንጓዴ መሰረተ ልማት ስራ የመዲናዋን አረንጓዴ ሽፋን ከ2 ነጥብ 8 በመቶ ወደ 20 በመቶ ማሳደግ ተችሏል። በመንገድ አካፋይና ዳርቻ፣ የህዝብ መናፈሻዎች፣ ዘላቂ ማረፊዎች፣ በግለሰቦች ግቢና አካባቢ፣ የወንዝና ዳርቻዎች፣ የክብረ በዓልና ፕላዛ ቦታዎች፣ የሃይማኖት ተቋማት ግቢና አካባቢ፣ ስፖርት ሜዳዎች፣ በሰፈር ውስጥ የሚገኙ ክፍት ቦታዎችና መሰል አካባቢዎች ትኩረት በመስጠት በችግኝና በተለያዩ ዕፅዋት የመሸፈን ስራ ተሰርቷል።

የልማቶቹ የጤና አበርክቶ

መጋቢት 28 ቀን ወይም በፈረንጆቹ አቆጣጠር አፕሪል 7፤ በየዓመቱ የዓለም የጤና ቀን ታስቦ ይውላል፡፡ ቀኑ የዓለም የጤና ድርጅት የተመሰረተበት ሲሆን፤ የህዝብ ጤና ትኩረት የሚሻ አጀንዳ ተመርጦ በዚያ ላይ ውይይት እየተደረገ ታስቦ ይውላል፡፡ ይህንን መነሻ በማድረግ አዲስ አበባ ከተማ እየተከናወኑ ያሉ ልማቶች በጤናው ዘርፉ በተለይም በሽታን በመከላከል የሚኖራቸውን ፋይዳ እንቃኛለን፡፡

በከተማዋ በቅርብ ዓመታት የተሰሩና በመሰራት ላይ የሚገኙ የኮሪደር ልማት፣ የወንዝ ዳርቻዎች ልማት፣ የአረንጓዴ አሻራ፣ የፓርክ፣ መናፈሻና መሰል የልማት ተነሳሽነቶች በጤናው ዘርፍ ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው እንደሆኑ በየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የአስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሮቮስት እና የህብረተሰብ ጤና ሳይንስ መምህር አቶ አለሙ ክብረት ይናገራሉ፡፡

አንደኛ ብዙዎቹ ተላላፊ በሽታዎች (ጉንፋን፣ አለርጂ፣ ቲቢ፣ ኮሌራና የመሳሰሉት)  ከንጽህና ጉድለት የሚመጡ ናቸው፡፡ ንጹህ አካባቢ መኖር ሁሌም ይመከራል፡፡ በትንሹ እንደ ጉንፋን፣ ቲቢ ያሉ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ የሚመጡ ተላላፊ ህመሞችን በሽታን የመከላከል አቅምን በማሳደግ ማስቀረት የሚቻሉ ናቸው፡፡ አካባቢን እና ወንዞችን ንፁህ የማድረግ ስራዎች ተላላፊ ህመሞችን ለመከላከል ትልቅ አቅም የሚሆኑ ናቸው ይላሉ፡፡

አቶ አለሙ እንደገለፁት፣ በኮሪደር ልማቱ የተሰሩ የእግረኛና ሳይክል መንገዶች፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎች፣ የህፃናት ማቆያዎች ተላላፊ በሽታዎችን በመከላከል ከፍተኛ ፋይዳ አላቸው። ህፃናት ከተወለዱ ጀምሮ አካላዊና አእምሯዊ ጤንነታቸው ላይ መሰራት ይኖርበታል፡፡ ከዚህ አንጻር የህፃናት መጫወቻዎች መኖር በአካልና አእምሮ ጤናማ የሆነ ትውልድ እንዲኖር ያደርጋል፡፡

ሰዎች በእግራቸውና ብስክሌት በመጠቀም የሚንቀሳቀሱበት ሁኔታ መፈጠሩም ተላላፊ ብቻ ሳይሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየጨመሩ የመጡትን ተላላፊ ያልሆኑ እንደ ልብ፣ ስኳር፣ የደም ግፊት፣ ኩላሊት፣ ጉበት ያሉ ህመሞችን ለመከላከል እንደሚያግዙም መምህሩ  ያነሳሉ፡፡

የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ የኮሪደር ልማቱ የህብረተሰቡን ጤና በማሻሻል ረገድ ስለሚኖረው አበርክቶ በተመለከተ ባለፈው ህዳር ወር ለአዲሰ ልሳን ዝግጅት ክፍል የሰጡት ማብራሪያ ይህንን ያጠናክራል፡፡ የኮሪደር ልማቱ በእግር እንቅስቃሴ የማድረግን እድል ስለሚሰጥ ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች እንዲጠበቁ በማድረግ ረገድ ትልቅ እድል ማምጣቱንም አብራርተዋል፡፡

ዶ/ር ዮሐንስ እንደገለፁት፣ ቀደም ሲል የነበሩት ተላላፊ ያልሆኑት በሽታዎች ቁጥራቸው እየጨመረ መጥቷል። 52 በመቶ የሚሆኑ በተመላላሽ ህክምና የሚመጡ ታካሚዎች ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች የተያዙ ናቸው። እነዚህን በሽታዎች መከላከል የሚቻለው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ ነው። ለዚህ ደግሞ የኮሪደር ልማቱ ሰዎች እንደልባቸው በእግራቸው የሚጓዙበት ምቹ የእግረኛ መንገድ እንዲኖር እድል በመፍጠሩ እየጨመረ የመጣውን ተላላፊ ያልሆነ በሽታ እንዲቀንስ በማድረግ ረገድ ትልቅ አበርክቶ ይኖረዋል፡፡

ንፁህ በሆነ አካባቢ መኖር የዜጎች ህገ መንግስታዊ መብት እንደሆነ ያነሱት ዶ/ር ዮሐንስ፣ እውነታው የሚያሳየው አዲስ አበባ ከተማ ንጹህና ለነዋሪዎቿ ምቹ አልነበረችም፡፡ ንጽህናው  ባልተጠበቀ ቦታ፣ መጸዳጃ ቤት በሌለባቸው እና እጅግ በተጠጋጋ ሁኔታ ውስጥ ባሉ አካባቢዎች ላይ የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተላላፊ ለሆኑ በሽታዎች ተጋላጭ ሆነው ቆይተዋል፡፡ በርካታ የመዲናዋ ሰፈሮች በቂ መጸዳጃ ቤት እና ቆሻሻ ማስወገጃ የሌላቸው ከመሆኑ የተነሳ አብዛኛው ነዋሪ ለበሽታ ተጋላጭነቱ ሰፊ ነበር። በተለይም ህብረተሰቡ ለተስቦ፣ ለአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት እንዲሁም ለቲቢ በሽታዎች ተጋላጭ ነበር። የዝናብ ወቅት ሲያልፍ ተፋፍጎ የሚኖር የማህበረሰብ ክፍል በጉንፋንና አለርጂ በመሳሰሉ የመተንፈሻ ቱቦ በሽታዎች እንዲጠቁ ያደርጋቸዋል።

የህብረተሰብ ጤና መምህሩ አቶ አለሙም፤ ቤቶቹ የተፋፈጉና ያረጁ መሆናቸው ለበሽታ መንስኤ ከመሆን ባሻገር በተለይ ተላላፊ በሽታዎች ሲያጋጥሙ ለመቆጣጠርና ማህበረሰቡን የጤና ትምህርት ለመስጠት የሚያስቸግሩበት ሁኔታዎች ያጋጥሙ እንደነበረ አንስተዋል፡፡

የወንዝና ወንዝ ዳርቻዎች ጽዳትን የተመለከትን እንደሆነ ከመኖሪያ ቤት፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና ፋብሪካዎች በሚወጡ ደረቅና የፍሳሽ ቆሻሻዎች ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ ጉዳት በሚያደርሱ ኬሚካሎች የተበከሉ እንደሆኑ የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያሳዩ አቶ አለሙ ያነሳሉ፡፡ ወንዞች አካባቢ የሚበቅሉ ሰብሎችን ስለምንበላ፣ በውሃዎቹ ስለምንታጠብ፣ በአካባቢያቸው ስለምንኖርና ስለምንበክላቸው ከቀላል እስከ ለረጅም ጊዜ የሚቆዩ ህመሞችን የሚያስከትሉ ናቸው፡፡ እንደ ከተማ ወረርሽኞች ሲያጋጥሙ የመጀመሪያ የበሽታ መንስኤ ተደርጎ ምርመራ የሚደረግባቸው ወንዞችና የወንዞች ዳርቻዎችን ነው፡፡ ከዚህ አኳያ አሁን ላይ የወንዝና የወንዝ ዳርቻዎች ንፁህና ፅዱ ለማድረግ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ትልቅ ትርጉም ያላቸው ናቸው፡፡

አቶ አለሙ እንደሚገለፁት፣ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም የከተማዋን የደን ሽፋን ለማሳደግ የሚደረገው ጥረትም ሌላው በሽታን በመከላከል ከፍተኛ ጥቅም የሚሰጥ ነው፡፡ አረንጓዴ አካባቢ ለሰው ልጅ ጤና እጅግ መሰረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ የሰው ልጅ መተንፈስና መኖር የሚያስችለውን ንፁህ አየር ማግኘት የሚችለው ከእፅዋትና አረንጓዴ አትክልቶች ነው፡፡ ትናንት እንደ ሀገርም ሆነ ከተማ በከፍተኛ ሁኔታ ያጋጠመውን የደን መጨፍጨፍና መመናመን የተለያዩ ተነሳሽነቶችን በመተግበር፣ አካባቢን አረንጓዴ የማድረግ ጥረት ሁሉም አካል እንዲሳተፍበት በማድረግ ትልቅ የአመለካከት ለውጥ እየመጣ ነው፡፡

በሽታን የመከላከል ስራዎች ውጤታማ የሚሆኑት ማህበረሰቡ ሲሳተፍበት እንደሆነ የሚያነሱት የህብረተሰብ ጤና መምህሩ አለሙ፣ ሰፊው ማህበረሰብ የጤናው ባለቤት ሆኖ እንዲጠብቃቸው ግንዛቤ መፍጠር ላይ መስራት ይገባል። በዚህ ረገድ የጤናው ዘርፍ እና ሌሎች ተቋማት በማስተማር ኃላፊነታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review