የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር ስለሽ ስህን፣ የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ እና የአለም አትሌቲክስ የኢንተግሪቲ ዩኒት ተወካይ በተገኙበት ከኤሊት አትሌቶች፣ ከአሰልጣኞችና ከማናጀሮች እንዲሁ ከማናጀር ተወካዮች ጋር በአበረታች ቅመሞች ወይም ዶፒንግ ዙሪያ የጋራ ውይይት ተካሂዷል።
በውይይቱ ላይም የፀረ-አበረታች ቅመሞች እንቅስቃሴው በተለይም የምርመራና ቁጥጥር ስራው የበለጠ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የተጠቆመ ሲሆን ለዚህም መንግስትና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ከፍተኛ ቁርጠኝነት እንዳላቸው ተመላክቷል።
ከዚህም ጋር በተያያዘ ቀደም ሲል የተጀመሩ ፕሮግራሞች እንደተጠበቁ ሆነው እ.ኤ.አ ከ2025 ጀምሮ በጎዳና ላይ ውድድር (Road Race) የሚሳተፉ አትሌቶች ትኩረት ተሰጥቷቸው የምርመራው (Registered Testing Pool) አካል እንደሚሆኑ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን (ETH-ADA) እና የአለም አትሌቲክስ የኢንተግሪቲ ዩኒትም በአዲስ መልክ የRoad Race የምርመራ ፕሮግራም ይጀምራሉ ተብሏል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ አትሌቶችና አስልጣኞች ለፕሮግራሙ ውጤታማነት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ የተላለፈ ሲሆን በተለይም በአድራሻ ምዝገባ (Whereabouts Information) እና በምርመራ ወቅት የሚከሰቱ ክፍተቶችን ትኩረት ሰጥተው እንዲያስተካክሉ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክቡር መኮንን ይደርሳል አሳስበዋል።
ከሁሉም በላይ ደግሞ አትሌቶች በንፅህና በመወዳደር የቀደምቶቻቸውን ታሪክ የማስቀጠል ኃላፊነት እንዳለባቸው ተገንዘብው የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል።
ከዚህም በተጨማሪ የህግ ጥሰት በሚፈፅሙ አካላት ላይ አስተዳደራዊ እርምጃና የወንጀል ተጠያቂነትን ጨምሮ ህግንና አሰራርን የማስከበር ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በውይይቱ ወቅት አፅንኦት ተሰጥቶታል።
አሰልጣኞችና አትሌቶችም በውይይቱ ወቅት በቀጣይ መስተካከልና የበለጠ መጠናከር የሚገባቸውን ጉዳዮች ማንሳታቸዉን ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል፡፡