የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ጉባኤን ፋይዳ ያለው ተቋም አድርጎ ማስቀጠል እንደሚገባ ተገለጸ

You are currently viewing የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ጉባኤን ፋይዳ ያለው ተቋም አድርጎ ማስቀጠል እንደሚገባ ተገለጸ

AMN – መጋቢት 28/2017

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዳኞች ጠቅላላ ጉባኤ በቢሾፍቱ ተካሂዷል።

በጉባኤው “በፌዴራል ስርዓት ውስጥ የሰበር ችሎት ሚናና አተገባበር ላይ ያተኮር” እና የሰበር ችሎት ውሳኔዎች ከክልል ፍርድ ቤቶች አንጻር እንዴት ይታያሉ” በሚል ሁለት ሰነዶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምህረት፣ ጉባኤው ከተሰጠው ተልዕኮ አንጻር የሚጠቀስ አበርክቶ እስካሁን አለማሳካቱን ጠቅሰው፣ በሌላ በኩል የጉባኤውን መቀጠል የሚደግፉ ወገኖች ህጎችን ከማሻሻል አንጻር የተሻሻሉ ደንብና መመሪያዎችን ስራ ላይ መዋላቸውን ከመከታተልና ከማረጋገጥ አኳያ የጎላ ሚና ስላለው አስፈላጊነቱ ላይ እንደማይደራደሩ ተናግረዋል።

ከተሳታፊዎች ስብጥር አንጻር የፌዴራልና የክልሎችን ተወካዮች ያካተተ መሆኑን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፣ ስለሆነም ጉባኤውን ፋይዳ ያለው ተቋም አድርጎ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።

የዘንድሮው ጉባኤ የትኩረት ርዕስ “የሰበር ችሎት ሚና እና አተገባበር” ላይ መሆኑን ጠቁመው፣ በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ገንቢ ሃሳቦች ይጠበቃሉ ብለዋል።

ሰነድ ያቀረቡት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ቀነአ ቂጣታ፣ ሀገራዊ ጉዳዮችን ለጋራ ዓላማ ማዋልና ማስተዳደር የፌዴራል ስርአት መርሆ መሆኑን ተናግረዋል።

በሀገሪቱ ህገ መንግስት ፍርድ ቤቶች በራሳቸው የመመራት ነጻ ስልጣን እንዳላቸው ጠቅሰው፣ ነገር ግን የፌዴራል እና የክልል ጉዳይ ላይ በተለይም የሁለቱ ተቋማት የዳኝነት የስልጣን ወሰን ላይ የህግ ክፍተቶች እንደሚስተዋሉ አንስተዋል።

አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የፌዴራል እና የክልሎች ፍርድ ቤቶች በመግባባት ላይ በተመሠረተ አሰራር ተልዕኳቸውን እየተወጡ ነው ሲሉም አስረድተዋል።

የሰበር ችሎት ዓላማ ተገቢነት የጎደለውን ፍርድ ተፈጻሚነት ማሳጣትና የሰበር ሰሚ ፍርድ ቤቱ የራሱን ውሳኔ መተካት መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ሌላኛው ሰነድ አቅራቢ ዳኛ ፊጣ ደቻሳ በበኩላቸው፣ በሰበር ችሎት ላይ የሚተረጎመው ህግ በፌዴራል መንግስት ደረጃ ስራ ላይ ያለው ስለመሆኑ አብራርተዋል።

ከተለያዩ ክልሎች የመጡ ዳኞች እና የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንቶች የህግ የበላይነት የተረጋገጠባትን ሀገር ለመገንባት እና ጠንካራ የፍትህ ስርዓትን ለማረጋገጥ ሀገር አቀፍ የዳኞች ጉባኤን ማጠናከር ወሳኝ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

በምትኩ ተሾመ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review