የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ቀዳሚ ትኩረት ከተሰጣቸው የኢኮኖሚ መስኮች መካከል አንዱ ነው- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ቀዳሚ ትኩረት ከተሰጣቸው የኢኮኖሚ መስኮች መካከል አንዱ ነው- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN-መጋቢት 29/2017 ዓ.ም

“ከሸማችነት ወደ አምራችነት” በሚል መሪ ሀሳብ ከተማ አቀፍ የኢትዮጵያ- አዲስ አበባ ታምርት የ2017 ዓ.ም የአምራች ኢንዱስትሪዎች አውደ ርዕይ ተከፈተ።

አውደ ርዕዩን የከፈቱት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፣ የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ቀዳሚ ትኩረት ከተሰጣቸው የኢኮኖሚ መስኮች መካከል አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።

አዲስ አበባ ከተማን የኢንዱስትሪ ማዕከል እናደርጋለን ስንል ፈጠራን በማበረታት እና አምራቾችን በመደገፍ ጭምር ነውም ብለዋል።

ፋይናንስ በማቅረብ፣ የመስሪያ ቦታዎችን በማመቻቸት፣ መሠረተ ልማትን በማሟላት እና አስፈላጊ ሞያዊ ስልጠናዎችን በመስጠት ለአምራቾች ድጋፍ እንደሚደረግም ነው ከንቲባ አዳነች ያስታወቁት።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ዘርፉን ከማነቃቃት ባለፈ በተለያዩ ምክንያቶች ምርት አቁመው የነበሩ ኢንዱስትሪዎች ወደ ምርታማነት እንዲመለሱ ማድረጉን የተናገሩት ከንቲባ አዳነች፣ በመጪዎቹ ዓመታት አምራች ኢንዱስትሪው የበለጠ እንዲያድግ እንሰራለን ብለዋል።

በመርሐ-ግብሩ ላይ የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል አምራች ኢንዱስትሪው በኢኮኖሚው ውስጥ መዋቅራዊ ሽግግር እንዲያመጣ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢንዱስትሪ ዘርፉ ገቢ ምርትን በመተካት፣ ኤክስፖርትን በማሳደግ፣ የስራ ዕድልን በመፍጠርና ተወዳዳሪ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ዘርፍ ውጤታማ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑንም ነው ሚኒስትሩ የገለጹት።

የኢንዱስትሪ ዘርፉን በመደገፍ እና በሁለንተናዊ ውጤታማ እንዲሆን በማስቻል ረገድ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተጠቃሽ ተግባር ማከናወኑንም ተናግረዋል ሚኒስትሩ።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው፣ አዲስ አበባ ከያዘቻቸው የልማት እቅዶች መካከል ለአምራች ኢንዱስትሪው ትኩረት በመስጠት ዘርፉ ለኢኮኖሚው እደገት የሚያደርገውን አስተዋፅኦ ማሳደግ ነው ብለዋል፡፡

በዚህም ለአምራቾች መሰረተ ልማት በማሟላት፣ የፋይናንስ እና ማሽነሪ አቅርቦት በማሳደግ እንዲሁም ማስፋፊያ ቦታዎችን በመስጠት የማያቋርጥ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡

ከተማዋን የኢንዱስትሪ ማዕከል የማድረግ እንቅስቃሴ አንዱ ተግባር ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ የሚካሄደው የኢትዮጵያ- አዲስ ታምርት እንቅስቃሴ መህኑንም ነው አቶ ጃንጥራር የገለጹት፡፡

የኢትዮጵያ – አዲስ አበባ ታምርት ንቅናቄ ሲዘጋጅ አምራቾች ምርታቸውን ለሸማቹ እንዲያስተዋውቁ፣ የገበያ ትስስር አንዲፈጽሙ፣ ሽያጭ እንዲያከናውኑ፣ በአጠቃላይ አምራቾች ከፍ ባለ መድረክ ተገኝተው ልምድ እንዲለዋወጡ የሚያደርግ መሆኑንም ነው አቶ ጃንጥራር የተናገሩት፡፡

ንቅናቄው ባለፉት ሶስት አመታት ሲካሄድ አመርቂ ውጤት ተገኝቶበታል፡፡

የዘንድሮው የኢትዮጵያ – አዲስ አበባ ታምርት ንቅናቄም ከባለፈው በቂ ልምድ የተወሰደበት እና በአይነቱም የተለዬ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

በአዲስ አለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እየተካሄደ በሚገኘው አውደ ርዕይ ከ250 በላይ አምራች ኢንዱስትሪዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

በሰብስቤ ባዩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review