በክልሉ የሰላምን መንገድ ባልተቀበሉ ታጣቂዎች ላይ እየተወሰደ ባለው የህግ ማስከበር እርምጃ ዘላቂ ሰላም እየሰፈነ ነው – የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ

You are currently viewing በክልሉ የሰላምን መንገድ ባልተቀበሉ ታጣቂዎች ላይ እየተወሰደ ባለው የህግ ማስከበር እርምጃ ዘላቂ ሰላም እየሰፈነ ነው – የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ

AMN – መጋቢት 30/2017

በኦሮሚያ ክልል የሰላምን መንገድ የመረጡ ታጣቂዎችን ከመቀበል ጎን ለጎን የሰላም አማራጭን ባልተቀበሉት ላይ እየተወሰደ ባለው የህግ ማስከበር እርምጃ ዘላቂ ሰላም እየሰፈነ መምጣቱን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሀላፊ አቶ ሀይሉ አዱኛ፤ በክልሉ የልማት እና የሰላም ግንባታ ስራዎች ውጤታማ በሆነ መልኩ እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ በተገኘው ሰላም ተቋርጠው የነበሩ የልማት ፕሮጀክቶች ዳግም መጀመራቸውን፤ ህዝቡም በሙሉ አቅሙ በልማት እንዲሳተፍ እድል እየተፈጠረ መምጣቱን ጠቅሰዋል።

በአዲስ መልክ የተዘረጋው የቀበሌ አደረጃጀትም ሰላምና ደህንነትን ከማረጋገጥ አንጻር ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ ባለፉት ወራትም በመሰረተ ልማት ዝርጋታ፣ ማህበራዊ ልማት ስራዎችን በማጠናከር፣ በፍትህ እና በገቢ አሰባሰብ በኩል የተሳካ ስራ ተሰርቷል ነው ያሉት።

ከሁሉም በላይ የክልሉ መንግስት ለሰላም የከፈተው በር ትልቅ ውጤት ማምጣቱን ገልጸው፤ ባለፉት ወራት በርካታ የቀድሞ ታጣቂዎች ወደ ሰላም መጥተው የተሃድሶ ስልጠና መውሰዳቸውን ገልጸዋል።

የግጭት አፈታት ሂደቱም በመንግስትና በህዝቡ ተከታታይ ጥረትና ነባሩን የኦሮሞ የገዳ ስርዓት ማእከል ባደረገ መልኩ ሲከናወን መቆየቱን ተናግረዋል።

የቀድሞ ታጣቂዎቹ የተሃድሶ ስልጠና ከወሰዱ በኋላ የስራ እድል እንዲመቻችላቸው እየተደረገ ሲሆን ከፊሎችም በመንግስት መዋቅር ውስጥ እንዲሳተፉ መደረጉን ተናግረዋል።

ታጣቂዎቹ ወደ ማህበረሰቡ ተቀላቅለው ኑሯቸውን ማሻሻል እንዲችሉና የክልሉን መንግስት የልማት ውጥኖች እንዲያግዙ እየተደረገ መሆኑንም አክለዋል።

በክልሉ የሰፈነውን ሰላም ዘላቂ ከማድረግ አንጻር በዚህ ዓመት የተዘረጋው የቀበሌ አደረጃጀት መዋቅር ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም አቶ ሀይሉ አስረድተዋል።

የቀበሌ አደረጃጀቱ ለህዝቡ የተቀላጠፈ የመንግስት አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ፣ የህዝቡን ተሳትፎ ማሳደግና ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ ታልሞ መተግበሩን አስታውሰዋል።

በዚህም በክልሉ በአዲስ መልክ በተዘረጉ የቀበሌ መዋቅሮች ህዝቡ ተደራጅቶ ለአካባቢው ሰላምና ደህንነት ዘብ እንዲቆም ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም ገልጸዋል።

በቀጣይም ህዝቡ በየአካባቢው ተደራጅቶ ሰላምና ደህንነትን ማረጋገጥ እንዳለበት ጠቁመው መንግስትም ወደ ሰላም ባልመጡ ታጣቂዎች ላይ የህግ ማስከበር እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ተናግረዋል።

በተወሰዱ የህግ ማስከበር እርምጃዎችም ሰሜን ሸዋ፣ ምስራቅ ሸዋ፣ ምዕራብ ሸዋ እንዲሁም በምስራቅ እና ምእራብ ወለጋ ዞኖች ሰላም እየተረጋገጠ መምጣቱን ገልጸዋል።

አሁንም የክልሉ መንግስት የሰላም ጥሪ ክፍት መሆኑን አረጋግጠው ህዝቡም ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ጥረቱን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ከሰባት ሺህ በላይ ቀበሌዎችን በአዲስ መልክ በማደራጀት ከ50 ሺህ በላይ ባለሙያዎች መመደቡ ተገልጿል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review