ኢትዮጵያ ባለፉት 9 ወራት ከወጪ ንግድ 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መግኘቷን የንግድ እና ቀጣናዊ ትሥሥር ሚኒስቴር ሚኒስትር ካሣሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ።
የንግድ እና ቀጣናዊ ትሥሥር ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት አመራሮች “ቀጣናዊ ትሥሥር እና ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት ለንግድ ዘርፍ ዕድገት” በሚል መሪ ቃል የ2017 በጀት ዓመት የ9 ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ በጥራት መንደር እያካሄዱ ነው።
ሚኒስትሩ ካሣሁን ጎፌ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፣ ባለፋት ዘጠኝ ወራት በትብብር እና በቅንጅት በመሠራቱ በንግዱ ዘርፍ በርካታ ስኬቶችን ተመዝግበዋል።
የንግድ ካባቢን የሥራ ምቹነት የማሳደግ እና የአሠራር ሥርዓቶች እንዲሻሻሉ መደረጉን የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ በኦንላይን ንግድ ምዝገባ እና ፊቃድ ለ2.6 ሚሊዮን ተገልጋዮች አገልግሎት መሰጠቱን አስታውቀዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ 2.2 ሚሊዮን የድረ ፍቃድ እንስፔክሽን መከናወኑንም ነው የተናገሩት።
የኑሮ ውድነት እና የዋጋ ግሽበትን ከመቀነስ አንጻር ባለፉት 9 ወራት 374 ተጨማሪ የሰንበት ገበያዎችን በማቋቋም 1476 ሰንበት ገበያዎች አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ገልጸዋል።
በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ክትትል ከሚደረግባቸው ወጪ ንግድ ምርቶች ከ595 ሚሊዮን ዶላር በላይ መገኘቱን የገለጹት ዶክተር ካሣሁን ይህም ከዕቅዱ አንጻር ከ98 ነጥብ 2 በላይ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የአለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የቀረበቸው ጥያቄ ውይይት መደረጉንና በቀጣይ ዓመት በየካቲት ወር አባል ለመሆን ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን መግጻቸውን ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የማኅበራዊ ትሥሥር ገፅ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።