“የድህረ እውነት ዘመን በዕውቀት እና በእውነት” በሚል መሪ ሀሳብ ሀገር አቀፍ የሚዲያ ባለሞያዎች የመጀመሪያ ዙር የአቅም ግንባታ ስልጠና በአዲስ አበባ መሰጠት ጀምሯል፡፡
ስልጠናው በአዲስ አበባ ከተለያዩ ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች ለተወጣጡ የሚዲያ ባለሙያዎች እና አመራሮች የተዘጋጀ ነው፡፡
በመርሀ ግብሩ መክፈቻ ንግግር ያደረጉት የብልፅግና ፓርቲ ዋና ፅ/ቤት የህዝብና ዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ዕውቀት፣ክህሎት እና እውነትን መሰረት በማድረግ የማይበገር የመረጃ ስርአትን መዘርጋት ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ ቁልፍ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
አሁን ላይ የሚፈጠሩ የመረጃ ግራ መጋባቶች በውሳኔ ሰጪነት ላይ ትልቅ ተፅኖን የሚያሳድሩ መሆናቸውን ያነሱት ሃላፊው የተዘጋጀው አገር አቀፍ የሚዲያ ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና ይህንን በዘላቂነት ለመቅረፍ አላማ ያደረገ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
ስልጠናው ነጠላ ትርክትን በማስቀረት ገዢና ህብረ ብራዊነትን በሚያጠናክሩ
ሁነቶች ላይ ያነጣጠረ መሆኑን ያነሱት ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ለተከታታይ ሦስት ቀናት በአዲስ አበባ ከሚሰጠዉ ስልጠና በተጨማሪ በመላው የሀገሪቱ ክፍሎች የሚቀጥል መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
አሁን ላይ ዘመኑ የፈጠረውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ውሸቱን እውነት የሚያስመስሉ መረጃዎች ባህል እየሆኑ መምጣታቸውን ያነሱት ደግሞ የአዲስ አበባ የብልፅግና ፓርቲ ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ ናቸው፡፡
ችግሩን ለመቅረፍ እውቀትን፣ክህሎትን እና እውነትን መሰረት ያደረጉ መረጃዎችን ማድረስ የሚዲያ ባለሙያው ሀላፊነት ሊሆን ይገባልም ብለዋል፡፡
በራሄል አበበ