በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የባህልና ስፖርት ጉዳዮች አማካሪ በአቶ ቀጄላ መርዳሳ የተመራ ልዑክ በዩጋንዳ እየተካሄደ ባለው 11ኛው የአፍሪካ ክልላዊ የዘላቂ ልማት ፎረም ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።
ፎረሙ ዛሬ የተጀመረ ሲሆን “በዘላቂ እና ሁሉን አካታች የሳይንስ እና መረጃን መሰረት ባደረጉ መፍትሄዎች የስራ እድል ፈጠራ እና የኢኮኖሚ እድገትን በማፋጠን፤የ2030 እና 2063 አጀንዳዎችን እውን ማድረግ” በሚል መሪ ሀሳብ ነው እየተካሄደ የሚገኘው፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ የኢኮኖሚክ ኮሚሽን ከዩጋንዳ መንግስት ጋር በመተባበር ፎረሙን በጋራ አዘጋጅተውታል።
የዩጋንዳ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ካጉታ ሙሴቬኒ ባደረጉት ንግግር የአፍሪካን ዘላቂ ልማት ለማፋጠን፣ አፍሪካ የጥሬ እቃ አቅራቢ ከመሆን ተላቃ፣ በእሴት የዳበረ ውጤቶችን ለዓለም ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚነቷን ማረጋገጥ እንደሚገባት ገልጸዋል።
ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ውህደትን ማጠናከርም የአፍሪካን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እንደሚያፋጥንም አመልክተዋል።
ፎረሙ እስከ ሚያዚያ 3 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚቆይ በካምፓላ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።