የተሀድሶ ስልጠና የወሰዱ የፌደራል ፖሊስ አባላት ተመርቀዋል፡፡
ዛሬ የተመረቁት የፌደራል ፖሊስ አባላት በተለያዩ ምክንያቶች ከስራ ተሰናብተው የነበሩ ሲሆን፣ ዳግም በመፀፀት ወደ ቀደመ ስራቸው ለመመለስ ጥያቄ ያቀረቡ እና ተፈቅዶላቸው በአዳይቱ ፓራ ኮማንዶ ማሠልጠኛ ማዕከል ስልጠናቸውን ሲከታተሉ የነበሩ የፖሊስ አባላት እንደሆኑ ተመላክቷል፡፡
በምረቃ ስነ-ሥነ ሥርዓት ላይ የሥራ መመሪያ የሰጡት የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መስፍን አበበ፣ ፖሊስ ለወንጀል መከላከልና ለወንጀል ምርመራ ሥራዎች ወሳኝ የሆኑ የቴክኖሎጂ ትጥቆችን በሚገባ በሟሟላት በርካታ የሪፎርም ሥራዎችን በትኩረት በመስራት በፖሊሳዊ ሥነ-ምግባር ተልዕኮውን እየተወጣ የመነሳት ዘመን ላይ መድረሱን ገልፀዋል።
ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ተመራቂዎቹ ለሕብረተሰቡ የተሟላ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ ትምህርትና ሥልጠናዎችን በመውሰድ መመረቃቸውን አብስረው፣ ወደ ሥራ ሲሰማሩ ሕግ የማስከበር ተልዕኮ በትጋትና በኃላፊነት መፈፀም እዳለባቸው የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡
ምክትል ኮሚሽነር ጀነራሉ አክለውም፣ ሥልጠናው እንዲሳካ አስተዋፅኦ ላደረጉ ለአፋር ብሔራዊ ክልል መንግሥት፣ ለአካባቢው ኅብረተሰብ እና ለሥልጠናው መሳካት የላቀ ተሳትፎ ላደረጉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ ሥር የዩንቨርስቲ ደኅንነት ፖሊስ መምሪያ የሰው ሃብት አስተዳደር ምክትል መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ዓለሙ ወንዳፍራሽ በበኩላቸው፣ ሰልጣኞቹ ተጸጽተው ወደ ተቋማቸው የተመለሱ በመሆናቸው የተሰጣቸውን ትምህርትና ስልጠና በሚገባ ተከታትለው ባሳዩት ፍፁም ዲሲፕሊን እና ፖሊሳዊ ጨዋነት በስልጠናው ማጠቃለያ በሀገር ፍቅርና በኢትዮጵያዊ አንድነት ታንጸው መውጣት እንደቻሉ ገልጸዋል።
ተመራቂዎች በበኩላቸው፣ ተቋማቸው ያደረገላቸውን ጥሪ እንደ ዕድል በመጠቀም የተከበረ የፖሊስ ሙያን በድጋሚ መቀላቀላቸው ለቀጣይ ሥራቸው ሞራል እና ተነሳሽነት እንደፈጠረላቸው ተናግረው፣ በቀጣይም የሚሰጣቸውን ማንኛውንም ግዳጅ በብቃት መወጣት የሚችሉ ብቁ ፖሊሶች እንደሚሆኑ መናገራቸውን ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የማህበራዊ የትስስር ገጽያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡