በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር እና በተጠሪ ተቋማቱ ሲያካሄድ የቆየውን የመስክ ምልከታ አጠናቋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወ/ሮ አሻ ያህያ የኦን ላይን ንግድ ፈቃድና ምዝገባ አገልግሎት አሰጣጥ፣ የኤክስፖርት ንግድ አፈፃፀም እና የወጡ አዋጆችን ተግባራዊ ከማድረግ አንፃር የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን አመላክተዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የኑሮ ውድነትንና የዋጋ ንረትን ከማስተካከል አኳያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት እንዳለበትም አሳስበዋል።
ከነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት አኳያ በመላ አገሪቱ የሚታየውን ቅሬታ ተከታትሎ በቅርበት መደገፍ እና በአጥፊዎች ላይ ተገቢው የእርምት ርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ ይኖርበታል፡፡
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጐፌ (ዶ/ር) ህገ ወጥ ኬላዎች መብዛትና ተደራራቢ ቀረጥ ለኤክስፖርት ንግዱ ተግዳሮቶች መሆናቸውን ጠቁመው፤ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት በጋራ መስራት ይገባል ማለታቸዉን ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያገኘነዉ መረጃ ያሳያል፡፡