ባለፉት ዘጠኝ ወራት 2ሺህ የሚሆኑ መካከለኛ ደረጃ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች መገንባታቸውን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ገለፁ።
የ2017 በጀት ዓመት የሦስተኛው ሩብ ዓመት የ100 ቀን አፈጻጸም እና የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራ የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተገምግሟል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ በሰጡት ማብራሪያ እንደገለጹት: ባለፉት ዘጠኝ ወራት የባህል ዲፕሎማሲ በባህልና ስፖርት ዘርፉ ከተሰሩ ስኬታማ ስራዎች መካከል የሚጠቀስ ነው።
ኢትዮጵያ ያላትን በርካታ ባህልና እሴት ለባህል ዲፕሎማሲ ከመጠቀም አንፃር ከተሰሩ ስራዎች መካከል እሴቶችን ያስተዋወቀችበት የምስራቅ አፍሪካ የባህልና ኪነጥበብ ፌስቲቫል አንዱ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በፌስቲቫሉ የምስራቅ አፍሪካ የባህል ሚኒስትሮች፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎችና የባህል ቡድኖች ባህላዊ እሴቶቻቸውን ማስተዋወቃቸውንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ያላትን ባህላዊ እሴቶች ለብሪክስ አባል ሀገራት ለማቅረብ ዝግጅት ላይ መሆኗንም ገልፀዋል።
በሀገሪቱ የስፖርት ልማትን ስኬታማ ለማድረግ ከህፃናትና ታዳጊዎች ጀምሮ ወጣቶችን ማዕከል በማድረግ መካከለኛ ደረጃ ያላቸው ሶስት በአንድ የሚባሉ ስታዲየሞች ተገንብተዋል ብለዋል።
በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት 2ሺህ የሚሆኑ መካከለኛ ደረጃ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች መገንባታቸውን ተናግረዋል።
ባለፉት ስድስት አመታት ከ10ሺህ በላይ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እድሳት መከናወኑንም አብራርተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በወሰዱት ኢኒሼቲቭ ከለውጡ በፊት ተጀምሮ ሲጓተት የነበረው የአደይ አበባ ስታዲየም ግንባታ ቀሪ ስራ ተለይቶ በሁለት ሎት ተከፍሎ ለኮንትራክተሮች መሰጠቱንም ገልፀዋል።
በየክልሉና አካባቢው ያሉ ከለውጡ በፊት ተጀምረው ሲንከባለሉ የነበሩ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ግንባታ መጀመሩን አንስተው በየክልሉ የአዳዲስ ትላልቅ ስታዲየሞች ግንባታ መጀመሩንም አስረድተዋል።
ብቁ ንቁ እና አሸናፊ ዜጋ ለመፍጠር ስፖርት የማይተካ ሚና ያለው በመሆኑ ስፖርትን ባህል ለማድረግ በከተሞች የማህበረሰብ አቀፍ -ማስ ስፖርት በየወሩ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
መንግስት ከመቼውም ጊዜ በላይ ለባህል፣ ኪነጥበብና ስፖርት በሰጠው ትኩረት ተጨባጭ ውጤት መታየት መጀመሩንም ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ባህላዊ እሴቶችን ለህዝቦች አብሮነት፣ ለጋራ ማንነትና አሰባሳቢ ትርክትን ለመገንባት በተሰሩ ስራዎች ከክልል እስከ ዞን ያሉ ኪነጥበብ ባለሙያዎች መሳተፋቸውን ጠቁመዋል።
ከሚያዝያ መጨረሻ ጀምሮ በብሪክስ አባል ሀገራት ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ኪናዊ ውጤቶችና ባህላዊ እሴቶችን በማስተዋወቅ የባህል ዲፕሎማሲን ማጠናከር የሚያስችል ስራ እንደሚሰራም ተናግረዋል።
በየአካባቢው ያሉ ባህላዊ እሴቶችን በተለይም ደግሞ ባህላዊ ፍርድ ቤቶችን ለህዝቦች አብሮነትና ለሰላም እሴት ግንባታ ለመጠቀም ከክልሎች ጋር የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
ተቋርጠው የነበሩ ስፖርታዊ ውድድሮችን የማስጀመር፣ የታዳጊ ወጣቶች ስፖርት እና የባህል ስፖርት ውድድሮች መካሄዳቸውን ተናግረዋል።
በግንቦት ወር የመላው ኢትዮጵያ ጨዋታ እንደሚደረግ አንስተው ስፖርት ከስፖርታዊ እንቅስቃሴ ባሻገር ማህበራዊ ትስስርንና አብሮነትን ለማጠናከር ያለውን ሚና ለማጠናከር የተጀመሩ ስራዎች እንደሚጠናከሩ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ስፖርት ለበርካቶች የስራ እድል መፍጠር የሚያስችል አቅም ያለው በመሆኑ የስፖርት አስተዳደር ስርዓት እንዲኖረው የተጀመሩ የህግ ማዕቀፍና የፖሊሲ ማሻሻያዎች እስከ መስከረም ይፀድቃሉ ነው ያሉት።
ስፖርት ከመዝናኛነት ባለፈ ለዜጎች የስራ እድል የሚፈጥርና የሀገር ገፅታ የሚገነባ መሳሪያ አድርጎ ለመጠቀም የሚያስችሉ ስራዎች በቀጣይ በልዩ ትኩረት የሚሰሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል።