ባለፉት ዘጠኝ ወራት በመዲናዋ ከተወለዱ ህጻናት 64 ሺ 75 የሚሆኑት በ90 ቀን ውስጥ የልደት ምዝገባ ማድረጋቸውን የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ አስታውቋል፡፡
የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ ጠቅላላ ካውንስል የ2017 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዋና ዋና የስራ አፈፃፀምን ገምግሟል፡፡
በአዲስ አበባ ህፃናትን በተወለዱ በ90 ቀናት ውስጥ በወቅቱ የልደት ምዝገባ ለማድረግ ኤጀንሲው በሰራው ስራ 64 ሺ 75 ህጻናትን መመዝገብ መቻሉን ገልጿል፡፡
እንዲሁም 528 ሺ 495 ነዋሪዎችን ወደ ዲጂታል ምዝገባ ማስገባት መቻሉ የተገለጸ ሲሆን ከአምናው 22 ነጥብ 54 በመቶ ብልጫ እንዳለውም ተመላክቷል ፡፡ይህም በዋናነት በ2016 ዓ.ም በማንዋል አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ 14 ወረዳዎች ሙሉ ለሙሉ ወደ ዲጂታል በመሸጋገራቸው የተገኘ ስኬት መሆኑ ተገልጿል።
በሌላ በኩል ለ339 ሺ 48 ነዋሪዎች የነዋሪነት መታወቂያ አገልግሎት በአዲስ ፣ በእድሳት፣ በእርማት እና በምትክ መሰጠቱም ተነግሯል፡፡
ከዚህም ውስጥ 97 ነጥብ 3 በመቶ ዲጅታል መታወቂያ የተሰጣቸው መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ቀሪው ለአቅመ ደካሞች እና ታማሚዎች የቤት ለቤት አገልግሎት ፣ የጣት አሻራቸው ለተጓዳ እንዲሁም አሻራ መስጠት ለማይችሉ አካል ጉዳተኞች የተሰጠ መሆኑን የኤጀንሲው መረጃ ያሳያል።