AMN – ሚያዝያ 09/2017
239 የሸማች የህብረት ስራ ልኳንዳ ቤቶች አንድ ኪሎ ስጋ ከ460 እስከ 520 ብር ብቻ እንዲሸጡ ተመን መቀመጡን የአዲስ አበባ ህብረት ስራ ኮሚሽን አስታወቀ።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ልእልቲ ግደይ የበአሉን የምርት አቅረቦትና የዋጋ ተመን በተመለከተ መግለጫ ተጥተዋል።
በዚህ መሰረትም በከተማዋ ዉስጥ ከእሁድ ገበያ በተጨማሪ 137 ባዛሮች በልዩ ሁኔታ በየአካባቢው በመክፈት ማሀበረሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ የግብርና እና የኢንደስትሪ ምርቶችን እንዲሸምት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል ።
154 መሰረታዊ ህብረት ስራ ማህበራትና 11 ዩኒየኖች ከተማዋ ላይ ያለዉን የኑሮ ዉድነት ለመቀነስ ባማከለ መልኩ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
800 የሚጠጉ የህብረት ስራ ማህበራት ሱቆች ለበአሉ ሙሉ አቅርቦትን በመያዝ እየሰሩ መሆናቸዉን ኮሚሽነሯ ገልጸዋል።
ለበአሉ የእርድ እንስሳት ወደ ከተማዋ እንዲገቡ በማድረግ 1 ኪሎ ስጋ ከ460 እስከ 520 ብቻ በማህበራቱ ልኳንዳ ቤቶች እንዲሸጥ በጥናት ተወስኗል ነው ያሉት።
ከዚህ በተጨማሪ በሁሉም የመሸጫ ቦታዎች የእንስሳት ተዋጽኦ ደረጃዉን በጠበቀና በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርብ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በሩዝሊን መሃመድ