እ.አ.አ በ1979 ለእይታ የበቃው ፊልሙ እስካሁን ከ2 ሺህ በሚበልጡ ቋንቋዎች ተተርጉሟል።
በዋነኛነት የሉቃስ ወንጌልን መሰረት አድርጎ የተሰራው ይህ ፊልም ፤ ከቅድመ ልደት እስከ እርገት ያለውን የኢየሱስ ክርስቶስን ታሪክ በወፍ በረር ያስቃኛል።
ዓለም ላይ በብዛት በመታየት ተወዳዳሪ ከማይገኝላቸው 10 የምንጊዜም ተወዳጅ ፊልሞች መካከል ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚሰለፈው ፊልሙ ፤ እ.አ.አ እስከ 2020 ድረስ ብቻ ከ8 ቢሊየን ጊዜ በላይ መታየቱ ይገመታል።
የፊልሙ ዳይሬክተሮች ፒተር ሳይክስ እና ጆን ክሪሽ ፤ ኢየሩሳሌም፣ ቴላቪቭ እና ጢባርያስ ከተሞችን ጨምሮ በመላው እስራኤል የተከናወነውን የፊልሙን ቀረፃ ለማጠናቀቅ በአጠቃላይ 31 ሳምንታት (8 ወር ገደማ) ፈጅቶባቸዋል።
Jesus ፊልም ከተውኔት ባሻገር ስለ ገጸ ባህሪያቱ እና ስለ ትዕይንቱ የድምፅ ማብራሪያ (ቮይስ ኦቨር) ያለው ሲሆን የእንግሊዘኛ ተራኪውም አሌክሳንደር ስኮርቢ ነው።
በ6 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በጀት ለእይታ የበቃው ፊልሙ ማጠናቀቂያው ላይ በተውኔት እና በፕሮዳክሽን ለተሳተፉ ባለሙያዎች ዕውቅና መስጫ መዘርዝር (ክሎዚንግ ክሬዲት) የለውም።
ይህም የሆነው የፊልሙ ዓላማ ወንጌሉን ወደ ምስል የመቀየር (የመተርጎም) ብቻ በመሆኑ እንደሆነ ፕሮዲዩሰሩ ጆን ሃይማን ተናግሮ ነበር።
1 ሰዓት ከ57 ደቂቃ ርዝማኔ ባለው በዚህ ፊልም ላይ ኢየሱስ ክርስቶስን ወክሎ የተጫወተው ኢንግሊዛዊው ተዋናይ ብሪያን ዲከን ሲሆን ተዋናዩ ገጸ ባህሪውን የመስራት ዕድል ያገኘው ከ900 ከሚበልጡ ሰዎች መካከል ተመርጦ ነው።
ፊልሙ ላይ የተለያዩ ቅዱሳንን ገጸ ባህሪያት በመጫወት በቢሊዮኖች ልብ ውስጥ ከቀሩ ተዋንያን መካከል ሪቭካ ኑማን (እንደ ቅድስት ድንግል ማርያም)፣ ዮሴፍ ሴሎአክ (እንደ ቅዱስ ዮሴፍ)፣ ኤሊ ኮሄን (እንደ መጥሞቁ ዮሐንስ)፣ ኒኮ ኒታይ (እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ) እና ታሊያ ሻፒራ (እንደ ማርያም መቅደላዊት) ይጠቀሳሉ።
በተቃራኒው ኢየሱስን አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮጡ ይሁዳን ገጸ ባህሪ ወክሎ የተጫወተው ኤሊ ዳንከር ፤ ፊቱ የክህደት መልክ ተደርጎ እስኪቆጠር ድረስ በተመልካቾች ዘንድ በእኩይነት ይታወሳል።